የወልድያ ነዋሪዎች  ለስታዲያም ማሰሪያና ለምረቃ በሚል ገንዘብ እንዲያዋጡ መገደዳቸውን ተናገሩ

ጥር ፪ (ሁለት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ባለሀብቱ ሼክ ሁሴን አላሙዲን በራሳቸው ወጪ ወልድያ ከተማ ላይ ዘመናዊ ስታዲየም እንደሚያስገነቡ በተናገሩት መሰረት፣ የስታዲየም ግንባታው ተጠናቆ ጥር 6 ቀን 2009 ዓም ይመረቃል። ምንም እንኳ ባለሀብቱ የግንባታውን ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍኑ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ የመንግስት ሰራተኛው የ1 ወር ደሞዙን በአመት፣ የከተማው ነጋዴዎችም እንዲሁ የተለያዩ መጠን ያላቸውን መዋጮዎች ሲከፍሉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ለስታዲየሙ ምረቃት በሚል የከተማው ነዋሪ ከ50 ብር ጀምሮ እንደ ኢኮኖሚ አቅማቸው  ገንዝብ እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው።

ነዋሪዎቹ “ ባለሃብቱ የስታዲየሙን ወጪ ሙሉ በሙሉ ሸፍኛለሁ ካሉ ህዝቡ ሲያዋጣ የኖረው ገንዘብ የት ደረሰ? “ የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም “ የወጣት ማእከል ይሰራበታል” ከማለት ወጪ  አጥጋቢ መለስ አላገኙም። በተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ሙስና እንደተፈጸመበት በመጥቀስ ፣ በገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሂሳቡ ተሰርቶ እንዲነገራቸው ፣  የዋጡት  ገንዘብ መጠን እስከ ባንክ ወለዱ ተሰልቶ ከተነገራቸው በሁዋላ በገንዘቡ ምን እናድርግበት በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚፈልጉ እየተናገሩ ነው።

ለምረቃው ዝግጅት 20 ሚሊዮን ብር የሚወጣ ሲሆን፣ አቶ ሃይለማርያም ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህን ያህል ገንዘብ ወጪ በማድረግ ምረቃውን ከማካሄድ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠቅም ነገር ሊሰራበት ይገባ ነበር በማለት ነዋሪዎች ትችት አቅርበዋል።

ብዛት ያላቸው የፌደራል ፖለስና ልዩ ሃይል አባላት በከተማው ተከማችተዋል። ወልዲያ ፊት ለፊት ያሉ ቤቶች ቤታቸውን በግዳጅ ቀለም እንዲቀቡ እየተደረገ ነው።