የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጉዳይ ሲመለከቱ የነበሩት ዳኛ ቢሚያም ዮሃንስ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አባላት ታፍነው መወሰዳቸው ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2009)

የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጉዳይ ሲመለከቱ የነበሩ የጎንደር ከተማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ዳኛ የሆኑት አቶ ቢኒያም ዮሃንስ ትላንት ማክሰኞ ከመስሪያ ቤታቸው በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አባላት ታፍነው መወሰዳቸውን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

ከወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ጋር በተገናኛ የኮሚቴው አባል የሆኑትን እና በእስር ላይ የሚገኙትን የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የክስ ጉዳይን በመዳኘት ላይ የነበሩ ዳኛ ቢኒያም በከተማዋ በሚገኝ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ታውቋል።

በቅርቡ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለችሎት በቀረቡ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተፈጸመባቸው መሆኑንና እጅና እግራቸውም በሰንሰለት ታስሮ መቆየቱን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ለአቤቱታቸው መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር ጉዳዩን የሚከታተሉ አካላት ለዜና ክፍላችን አስረድተዋል።

አቤቱታቸውን የሰሙት ዳኛ ቢኒያም ዮሃንስ ተከሳሽ ያቀረቡት የመብት ጥያቄ እንዲከበር በማዘዝ እጅና እግራቸው እንዲፈታ ትዕዛዝ አስተላልፈው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

የጎንደር ከተማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎትን በዋና ሰብሳቢነት የሚመራ ዳኛ ቢኒያም በኮማንድ ፖስት ለእስር ተዳርገው የነበሩ 21 ሰዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ውሳኔ አስተላልፈው እንደነበር እማኞች አክለው ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ፖሊስም ሆነ የፌዴራል ባለስልጣናት በዳኛው መታሰር ምክንያት የሰጡት መረጃ ባይኖርም ዳኛው ከስራቸው ጋር በተገናኘ ለእስር ሳይደረጉ እንዳልቀሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት ሃምሌ ወር በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ሰላማዊና ህጋዊ ዕልባት እንዲያገኝ ጥያቄ መቅረቡ ይታወሳል።

የወልቃይት ጠገዴ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከዚህ ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ ከወራት በፊት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ማክሰኞ ከመስሪያ ቤታቸው ታፍነው የተወሰዱት ዳኛ ቢኒያም ዮሃንስ የኮሎኔሉንና በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ በመመልከት ላይ እንደነበሩም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።