የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግፊትን እንዲያደርግ ተጠየቀ

ኢሳት (ጥቅምት 18 ፥ 2009)

የካናዳ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ልማታዊ ትብብር በመጠቀም በሃገሪቱ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግፊትን እንዲያደርግ የካናዳ የፓርላማ አባላት ጠየቁ።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ወደ 1ሺ 600 አካባቢ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሱት የፓርላማ አባላቱ የካናዳ መንግስት ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም እርምጃ እንዲወስድ ፒተር ኪንግ የተባሉ የፓርላማ አባል አሳስበዋል።

ለሃገራቸው መንግስት የጽሁፍ መልዕክትን ያቅረቡት የፓርላማ አባሉ፣ ካናዳ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ ለዴሞክራሲ መከበር ስትል ተጽዕኖን ለማድረግ በአማራጭነት መመልከት እንደሚገባት ጠይቀዋል።

“ሁሉም ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነቱ ተጠብቆ መኖር ይኖርበታል” ሲሉ በጽሁፋቸው ያመለከቱት ፒተር ኬንት በህግ የበላይነት የሚያምን መንግስት ብቻ ይህንን ስርዓት ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚችል አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት አዋጁ የሰብዓዊ መብት ረገጣን ያባብሳል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

አሜሪካ በተለየ መልኩ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያን የሰጠች ሲሆን፣ የሃገሪቱ ዕርምጃ በሌሎች አለም አቀፍ አካላት ዘንድ ስጋት መፍጠሩ ይነገራል።

መቀመጫቸውን በካናዳ ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ዕርምጃን መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ ዘመቻ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን CBC የተሰኘ የሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ከሽብርተኛ ድርጊት ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርጎ የሚገኝ አንድ ካናዳዊ ለማስለቀቅ የካናዳ መንግስት ማንኛውንም ጫና ማድረግ እንዳለበት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ባሽር ማክታል የተባለው ካናዳዊ ወደ ሶማሊያ ባቀና ጊዜ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ በሽብርተኛ ወንጀል ክስ የእድሜ ልክ ዕስራት እንደተላለፈበት ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የሃገሪቱ የፓርላማ አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጫናን በማሳደር ግለሰቡ እንዲለቀቅ የሚተየቅ ዘመቻን እያካሄዱ እንደሆነ ታውቋል።