የኢድ አልድሃ አረፋ በዓል ዛሬ በመላው ዓለም ተከበረ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 26/2009) የኢድ አልድሃ አረፋ በዓል ዛሬ በመላው ዓለም ተከበረ።

ለ1438ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢድ አለድሃ በዓለ በተለይ የሙስሊሞች መዲና በሆነችው መካ ከ2ሚሊየን በላይ ተጓዦች ከመላው ዓለም በመሰባብሰብ ማክበራቸው ታውቋል።

በዓሉ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያም የተከበረ ሲሆን እዚህ በዋሽንግተን ዲሲና በአካባቢው በፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የኢድ አል አድሃን በዓል ማክበራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ለዘንድሮ የሃጂ ጉዞ ለ15ሺህ ያህል ተጓዦች ፍቃድ ከሳዕዲ አረቢያ መንግስት ቢሰጥም ተመዝግቦ መሄድ የቻለው ግን ከግማሽ በታች መሆኑ ታውቋል።
ዛሬ በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው በዓል የመስዋዕት በዓል ይባላል።

ሼህ ካሊድ መሀመድ ዑመር በዋሽንግተን ዲሲ የፈረስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ኢማም በዓሉን አስመልክቶ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት ይህ በዓል ለፈጣሪ የሚገባውን ክብርና ታዛዥነት ለማሳየት አባት ልጃቸውን መስዋዕት አድርገው ያቀረቡበትን ሃይማኖታዊ መገልጪያ የሚወደስበት በዓል ነው።

በኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ወቅት እርድ በብዛት የሚከናወንበት እንደሆነ የሃይማኖቱ አዋቂዎች ይናገራሉ።
እንደየአካባቢው ሁኔታ ግመል፣ ፍየል፣ በግና በሬ ለእርድ ቀርበው መስዋትነቱን በሚያንጸባርቅ መልኩ የሚዘከርበት ዕለት ነው።

በኢትዮጵያም ዕለቱን ሃይማኖታዊ ይዘቱን በመጠበቅ ድሆችን በመመገብ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ ለታረዙት በማልበስና ለፈጣሪ የሚገባውን ክብር በመስጠት የሚከበርበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በዓሉ በዛሬ ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች መከበሩን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ በፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን አዘጋጅነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች በሮክ ክሪክ ፓርክ ተሰባስበው ያከበሩ ሲሆን የፈረስት ሂጅራ ፈዋንዴሽን ኢማም ሼህ ካሊድ መሀመድ ዑመር የጸሎት ፕሮግራሙን በመምራት የዕለቱን አብይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢድ አል አድሃ በዓል በተለይ የእስልምና እምነት የፈለቀባትና የዓለም ሙስሊሞች መዲና በሆነችው መካ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። ዘንድሮም ከ2ሚሊየን በላይ የእምነቱ ተከታዮች በበዓሉ ስፍራ ተገኝተው በሃይማኖታዊ ስነስርዓት ማክበራቸው ተዘግቧል።

ለ3ቀናት በተለያዩ ሃይማኖቱ በሚያዛቸው ስፍራዎች በመገኘት የሚጠበቅባቸውን የሚያደርሱት ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ተጓዦች በመጨረሻው ቀን የኢድ አል አድሃ በዓል ዛሬ በመካ መዲና በሚገኝ ሃይማኖታዊ ስፍራ በሰይጣን የሚመሰልን ግዙፍ ህንጻ በድንጋይ በመደብደብ ለጌታቸው ያላቸውን ታማኝነት በማሳየት የሚያከብሩት እንደሚሆን ተገልጿል።

ለዚህ በዓል በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች ወደ መካ የሚያመሩ ሲሆን ዘንድሮ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ተጓዥ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማቅናቱን ለማወቅ ተችሏል።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ በዘንድሮው በዓል ለኢትዮጵያ ለ15ሺህ ተጓዦች ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ፈቃድ የተገኘ ቢሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት መጅሊሱ ያገኘው ተጓዥ ቁጥር ግን ከ7ሺህ 500 በታች መሆኑ ታውቋል።

ለዚህም ሁለት ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ የገለጹት የኢሳት ምንጮች ዘንድሮ ባልተለመደና ከሃይማኖቱ መስመር ውጪ ወደ ሳዕዲ አረቢያ የሚደረገው የሃጂ ጉዞ በትግራይ ክልል ማለፍን እንደቅድመ ሁኔታ ማስቀጡ የተጓዦች ቁጥር እንዲቀንስ አድርጓል ተብሏል።

በሌላ በኩል ለሃጂ ጉዞ ቀደም ሲል ይከፈል የነበረው የገንዘብ መጠን በዘንድሮ ከ20ሺህ ብር በላይ መጨመሩ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ስለተፈታተነው ወደ ስፍራው እንዳይጓዙ እንዳደረጋቸው ይነገራል።

በፊት ለሃጂ ጉዞ 55ሺህ ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ዘንድሮ በመጅሊሱ በተደረገ ውሳኔ 79ሺህ ብር እንዲሆን መድረጉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።