የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ ወደ ናይጀሪያ ከሚጓዙ መንገደኞች ህገወጥ ተጨማሪ ክፍያን ሲቀበል እንደነበር ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 14 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ በኩል ወደ ናይጀሪያ ከሚጓዙ መንገደኞች በአንድ ተጓዥ እስከ 150 ዶላር የሚደርስ ህጋዊ ያልሆነ ተጨማሪ ክፍያን ሲቀበል ቆይቷል ሲል የናይጀሪያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንን ቅሬታ አቀረበ።

የባለስልጣኑ ሃላፊ የሆኑት ሳም አድሮግቦዬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይጀሪያውያን መንገደኞች ተመላሽ የማይሆን የዲፖርቴሽን ክፍያን ለረጅም አመታት ሲሰበሰብ መቆየቱን ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። ከሌጎስና አካኑ ኢቢያም አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያዎች ተነስተው በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካዊቷ ጆሃንስበርግ ከተማ የሚያቀኑ መንገደኞች ከ75 እስከ 150 ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉን ዘኔሽን የተሰኘ ጋዜጣ ሃላፌውን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

ክፍያውን መክፈል ያልቻሉ መንገደኞች ከደቡብ አፍሪካ በግዳጅ ተመላሽ ሲሆኑ ሃላፊነቱን እንወስዳለን ብለው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ፊርማ እንዲፈርሙ መደረጉንም የናይጀሪያ የሲቪል አቪየሽን ኤጀንሲ አስታውቋል።

ከናይጀሪያ ተነስተው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙ መንገደኞች የአንድ ቀን ቆይታ ካጋጠማቸው ክፍያው 75 ዶላር መሆኑ ቀርቶ 150 ዶላር እንዲከፍሉ ሲደረግ መቆየቱንም የባለስልጣንኑ ሃላፊ ሳም አዱሮግቦዬ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ከበርካታ ናይጀሪያውያን መንገደኞች የቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምርመራ ሲካሄድበት ቆይቷል ያሉት ሃላፊው በዚሁ ምርመራ ህገወጥ ነው ያሉት ክፍያ ተፈጻሚ ሆኖ ሊገኝ መቻሉን አክለው ገልጸዋል።

የተጨማሪው ክፍያ መታወቅን ተከትሎም የናይጀሪያ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በሃገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካዮችን አስጠርቶ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር ማካሄዱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካዎች ክፍያው ከናይጀሪያውያን መንገደኞች ሲሰበሰብ መቆየቱን አረጋግጠው ከደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ ያልተደረጉ መንገደኞች የከፈሉት ክፍያ ተመላሽ ተደርጎላቸዋል የሚል ምላሽ መስጠታቸው ዘኔሽን ጋዜጣ በሪፖርቱ አስነብቧል።

ይሁንና የናይጀሪያው የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ክፍያው ተቀባይነት የሌለውና የባለስልጣኑ አሰራር እና መመሪያ የጣሰ ድርጊት ነው ሲል ተቃውሞን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእንግዲህ በኋላ የናይጀሪያውያን መንገደኞችን እንዲህ ያለ ክፍያን እንዳያስከፍል ማሳሰቡንም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አየር መንገዱ በመንገደኞች ትኬት ላይ የዋጋ ጭማሪን ማድረግ ከፈለገ እንኳን ጭማሪውን በቅድሚያ ለባለስልጣኑ ማቅረብ እንዳለበትና ዕውቅና ማግኘት እንደሚጠበቅበት የናይጀሪያ ባለስልጣናት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ካሉት ሰፊ የገበያ ድርሻዎች መካከል ናይጀሪያ ዋነኛው እንደሆነ ይነገራል።