የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በአሜሪካ ያለክፍያ የመውለድ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የአሜሪካ ኤምባሲ ገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ለጉብኝት በሚል ወደ አሜሪካ በመሄድ ያለምንም ክፍያ የመውለድ አገልግሎት ማግኘታቸው ስጋት እንዳሳደረበት ገለጸ።

ኤምባሲው ለአየር መንገዱ ባቀረበው አቤቱቷ ወደ አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት ተጉዘው ማንኛውንም ህክምና ያደረጉ ሰራተኞችን በተመለከተ ሪፖርት እንዲያደርጉለት ጥያቄ ማቅረቡን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

ኤምባሲው ለእረፍት በሚል ወደ ሃገሪቱ ሄደው የመውለድ እና የተለያዩ አገልግሎት ያገኙ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ዝርዝር በእጇ እንደሚገኝም ገልጿል።

የኤምባሲው ሰራተኞች በእጃቸው የሚገኝ የአሜሪካ የመግቢያ ቪዛን ለማደስ በሚሄዱ ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ በአግባቡ ጉዳዩ ለሚመለከተው ክፍል እንዲያስረዱም አሳስቧል።

ይህንን በማያደርጉ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ላይ ወደ አሜሪካ እድሜ ልክ እንዳይገቡ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ኤምባሲው ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል።

በአሜሪካ የመውለድ እና ሌላ የጤና አገልግሎት ያገኙ ሰራተኞች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ያለባቸው የህክምና ክፍያ እንዲከፍሉ እንደሚያደርግም የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በበኩላቸው ኤምባሲው ያቀረበው አቤቱታ ተገቢ መሆኑን አረጋግጠው፣ በርካታ ሰራተኞች የሚወልዱት ልጅ የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ በማሰብ ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ አስረድተዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ ወደሃገሪቱ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ጠንካራ የቪዛ መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። ይሁንና፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ላይ የቀረበው ቅሬታ የመጀመሪያው መሆኑ ተነግሯል።

ስማቸው ያልተገለጸ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ ኤምባሲ የመግቢያ ቪዛን ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤምባሲው ላቀረበው ቅሬታ ምላሽ ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ ኤምባሲው ምን ያህል በሰራተኞችና የቤተሰብ አባላት የመውለድና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን በነጻ እንዳገኙ የገለጸው ነገር የለም።

የአየር መንገዱ የሰው ሃብት ክፍል በበኩሉ ሰራተኞቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቡም ተመልክቷል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 አም ኤምባሲው ለ18 ሺ ሰዎች የመግቢያ ቪዛን የሰጠ ሲሆን፣ ወደ 11ሺ አካባቢ ሰዎች ደግሞ የመኖሪያ የመግቢያ ቪዛ መስጠቱ ታውቋል።

ይሁንና ኤምባሲው የሚከለክለው የቪዛ ጥያቄ መጠን እስከ 60 በመቶ አካባቢ መድረሱንም ለመረዳት ተችሏል።