የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም 15 በመቶ እንዲቀንስ ተወሰነ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010) የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም 15 በመቶ እንዲቀንስ በመወሰኑ ከነገ ጥቅምት 1/2010 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ።

በዚህም አንድ የአሜሪካን ዶላር በ27 የኢትዮጵያ ብር እንደሚመነዘር ተመልክቷል።

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መስከረም 29/2010 ሲጀምር ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ መወሰኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህም ኤክስፖርትን ለማበረታታት ታልሞ መሆኑን በንግግራቸው ቢጠቅሱም ርምጃው ግን የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ከጥቅምት 1/2010 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው የብር የመግዛት አቅም መቀነስ አንድ የአሜሪካን ዶላር አሁን ካለበት የ23 ብር ምንዛሪ ወደ 27 ብር ከፍ ይላል።

በዩሮና በፓውንድ እንዲሁም በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ ለውጥ እንደሚኖር ታውቋል።

ኢሳት የውስጥ ምንጮችን በመጥቀስ ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 16/2010 ባቀረበው ዘገባ መንግስት የብር ዋጋን ለመቀነስ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቆ ነበር።

የብር ዋጋን ከ10 እስከ 15 በመቶ ለመቀነስ የተደረገውን ጥናት የመሩት የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉና ምክትላቸው አቶ ዮሀንስ አያሌው መሆናቸውንም ኢሳት መዘገቡ አይዘነጋም።

የንጉሱ ስርአት በ1966 ከስልጣን ሲወገድ አንድ የአሜሪካን ዶላር በ2 ብር ከ07 ሳንቲም ይመነዘር እንደነበር የአለም ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ።

የደርግ መንግስት እስከ ወደቀበት እስከ 1983 ይህው 2 ብር ከ07 ሳንቲም የአንድ ዶላር ህጋዊ ምንዛሪ ሆኖ ቆይቷል።

ንጉሱ ከስልጣን ሲወርዱ በጥቁር ገበያ የነበረው ወይንም ህገ ወጡ ምንዛሪ ለአንድ ዶላር 3 ብር ከ34 ሳንቲም ነበር።

የደርግ መንግስት ሲወድቅ ሕጋዊው ምንዛሪ 2 ብር ከ07 ሳንቲም ቢሆንም በጥቁር ገበያ የነበረው ግን 7 ብር እንደነበር የአለም ባንክ መረጃ ያስታውሳል።

ደርግ ከስልጣኑ ሊወገድ 5 አመት እስኪቀረው የጥቁር ገበያው ምንዛሪ 4 ብር አካባቢ ላይ ቆይቷል።

ስርአቱ እየተዳከመና አማጽያኑ እየገፉ ሲመጡ የጥቁር ገበያው ወደ 7 ብር ከፍ ማለቱ ተመልክቷል።

የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ በአመቱ ህጋዊውን ምንዛሪ ከ2 ብር ከ07 ሳንቲም ወደ አምስት ብር ከፍ ያደረገው ሲሆን በጥቁር ገበያ 7 ብር ከ40 ሳንቲም ይመነዘር ነበር።

በ1997 ምርጫ ወቅት ህጋዊው ምንዛሪ 8 ብር ከ65 ሳንቲም የነበረ ሲሆን ህገ ወጡም በተመሳሳይ መጠን በሳንቲም ልዩነት ውስጥ ነበር።

ከዚህ በኋላ የውጭ ምንዛሪው ከቁጥጥር ውጭ እየሄደ ዛሬ የደረሰበት 23 ዶላር ላይ መድረሱ ተመልክቷል።

በአዲሱ ምንዛሪ ደግሞ የአንድ የአሜሪካን ዶላር ከነገ ጀምሮ በ27 ብር የሚመነዘር ይሆናል።