የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና ምክትላቸው ከሃገር ኮበለሉ

ኢሳት (መጋቢት 11 ፥ 2009)

የበርካታ ሚሊዮን ብር ብክነት ሪፖርት የቀረበባቸው የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሃገር መኮብለላቸውን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። ሁለቱ ባለስልጣናት ከሃገር የኮበለሉት ስራቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

ባሳለፍነው ታህሳስ ወር የ16 ሚሊዮን 863 ሺ 33 ብር ከደምብ ውጭ ህገወጥ የመድሃኒት ግዢ ፈጽመዋል በሚል በፓርላማ ሪፖርት የቀረበባቸው ዋናው ዳይሬክተር አቶ መስቀሌ ሌራ እና ምክትላቸው ምርመራ ከተጀመረባቸው በኋላ በቦሌ በኩል በህጋዊ መንገድ ከሃገር መውጣታቸው ታውቋል።

በአለም አቀፍ ድርጅቶችና የውጭ መንግስታት ድጋፍ የሚደረግለት የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ከተመሰረተ እኤአ ከ2007 ጀምሮ ከፍተኛ ምዝበራ ሲካሄድበት መቆየቱም ተመልክቷል። በታህሳስ ወር 2009 ለፓርላማ በቀረበ በጠቅላይ ኦዲተር ሪፖርት በህገወጥ አሰራር ወደ 17 ሚሊዮን ብር በማውጣት የተወነጀሉት ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች፣ ለጤና ተቋማት መሰራጨት የነበረባቸው የ569 ሚሊዮን 833ሺ 919 ብር ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ሳይሰራጩ በመገኘታቸውም ተጠያቂ መሆናቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ከለጋሾች የተገኘ ወደ መቶ ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ብር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማባከን ስማቸው የተነሳው የኤጀንሲው ሃላፊዎች ወዲያውኑ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁ ቢሆንም፣ ምርመራ ከተጀመረባቸው በኋላ ሃገር ጥለው መጥፋታቸው ተመልክቷል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መስቀሌ ሌራ እና ምክትላቸው ምርመራ ከተጀመረባቸው በኋላ ከሃገር ህጋዊ በሆነ መንገድ የወጡት ተባባሪዎቻቸው በሆኑት የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ብክነት የዳረጉት የልማት ባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ባህረም በተመሳሳይ ምርመራ ከተጀመረባቸው በኋላ በህጋዊ መንገድ ከሃገር መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።