የኢሳት 7ኛ አመት በሙኒክ ጀርመን በተሳካ ሁኔታ ተከበረ

ሚያዝያ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢሳት አለማቀፍ የድጋፍ ኮሚቴ የበላይ መሪነት እና በሙኒክ የኢሳት ቤተሰቦች የተዘጋጀው የኢሳት 7ኛ አመት የልደት በአል በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አዘጋጆች ገልጸዋል።
በእለቱ የክብር እንግዳ ሆነው የቀረቡት ከአሜሪካ የቢቢኤን ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድና የኢሳት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ነበሩ። ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ ፣ ባለፉት 25 አመታት የህወሃትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ገፍና መከራ ዘርዝሮ ያቀረበ ሲሆን፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን መታገል የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጾአል። “ በኦሮሞ ተደራጅተን ታግለን አይተነዋል፣ በአማራ ተደራጅተን ታግለን አይተነዋል፣ በሃይማኖት ተደራጅተን ታግለን አይተነዋል፣ ከእንግዲህ ትግላችን በኢትዮጵየዊነት ስም ሆኖ መካሄድ አለበት ያለው ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ፣ በሰበብ አስባቡ መከፋፈላችን በደሉንና ጭቆናውን ከማራዘም ውጪ የሚጠቅም ነገር እንደሌለው በአጽንኦት ገልጾአል።
ጋዜጠኛ ሳዲቅ ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ ባቀረበው ንግግር ተሳታፊዎች አድናቆታቸውን በከፍተኛ ጭብጨባ ገልጸውለታል።
ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም የመጣንበትና የምንሄድበት በመንገድ በሚል ባቀረበው ንግግር ደግሞ ኢሳት ከምስረታው እለት ጀምሮ የተጓዘበትን መንገድ በማሳየት፣ የህወሃት አህአዴግ የአፈናና የግድያ ስርዓት እንዲያበቃ ኢሳት የተጫወተውን ሚና የተለያዩ የድምጽ ማስረጃዎችን በማቅረብ አሳይቷል። የመጣንበት መንገድ እንዳለ ሆኖ፣ ወሳኙ ከዚህ በሁዋላ የምንሄድበት መንገድ በመሆኑ ፣ መንገዳችንን በጥንቃቄ፣ በብልጠትና በጽናት እንዴት መጓዝ አለብን በሚለው ጉዳይ መምከር እንደሚገባን አሰረድቷል። አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ “ አሮጌው ስርዓት እየሞተ ነው፣ አዲሱ ስርዓት ግን እየተወለደ አይደለም” በሚል የአንቶኒዮ ግራማሺ ንግግር ሃሳቡን ያካፈለው ጋዜጠኛ ፋሲል፣ ጊዜው አዲስ ስርዓት እንዲወለድ የምንሰራበት በመሆኑ፣ ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ ልንረባረብ ይገባል ብሎአል።
እንግዶች ከተናገሩ በሁዋላ ከቤቱ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል። ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳዩ ግጥሞችን አቅርበዋል።
የሙኒክ የኢሳት የሴቶች ግብረሃይል ያዘጋጀው መስተንግዶ በታዳሚው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።
በለቱ ተዘጋጅቶ የነበረውን ጨረታ አሸናፊ የሆኑት አቶ አበበ ተሰማ ሽልማታውን ወሰደዋል። ታዳሚዎች በየዝግጀቶች መሃልና በዝግጅቱ መጨረሻ በአገራዊ ዜማዎች ተዝናንተዋል።