የአቶ ሃይለማርያምና ባለቤታቸው የቤተክርስቲያን ጉብኝት ምዕመናን አስቆጣ

ግንቦት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኃ/ማርያም ደሳለኝ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሮማን ተስፋዬና ከሌሎች ባለሳልጣናት ጋር በእስራኤል በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ባደረጉት ጉብኝት የቤተክርስቲያኒቱን ስርዓት አለመጠበቃቸው በርካታ ምዕመናንን አስቆጣ።
አቶ ኃ/ማርያምና ባለቤታቸው የሌላ እምነት ተከታይ ቢኾኑም አብያተ ክርስቲያናቱን መጎብኘት እንደሚችሉ በመጥቀስ ሆኖም በጉብኝታቸው ወቅት ”ከሀይማኖቱ አስተምህሮና ቀኖና ውጪ ከነጫማቸው መቅደስ ውስጥ መግባታቸው አምላክን ብቻ ሳይሆን እኛን የቤተክርስቲያኗን ተከታዮችም መናቅ ነው” በማለት ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ለዚህም ተጠያቂዎቹ አቶ ኃይለማርያምና ባለቤታቸው ብቻ ሳይሆኑ ወደ መቅደሱ ለጉብኝት የጋበዟቸው የህወኃትና የብአዴን አባላት የሆኑ ካህናት ጭምር ናቸው ሲሉ በእስራኤል ያሉ የቤተክርስቲያኗ ልጆች ይከሣሉ።
ቤተክርስቲያናችን “የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” የሚለውን የመጽሀፍ ቃል ከነገሥታቱ ዘመን አንስቶ በፈሪሀ እህዚአብሔር ስታከብረው ቆይታለች የሚሉት ምዕመናን፤ በታላላቅ ነገሥታቶች ያልተፈጸመ ድፍረትን በአቶ ኃይለማርያም እንዲፈጸም ያደረጉ ካድሬ አገልጋዮች ቦታውን ሊለቁ ይገባል ብለዋል።
አቶ ኃይለማርያም በእስራኤል ባደረጉት ጉብኝት ከፍ ያለ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ይታወቃል።