የአባይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ተገለፀ

ጥር 4 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-አቶ መለስ ዜናዊ “ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንኛዉንም መስዋዕትነት ይከፍላል፡ በአንድ ቃል ‘ ግድቡ ይሰራ!’ እንደሚሉ ምንም ጥርጥር የለኝም” በማለት የተናገሩ ቢሆንም ፣ ዜጎች በአብዛኛዉ በግንባታዉ ስራ ደስተኛ እንዳልሆኑ ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተርስ ዘገበ።

አገሪቱ በራሷ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ብላ የተያያዘችዉና ያደረባት ጉጉት ከሚገባዉ በላይ መጠኑን ያለፈ መሆኑ እና ፕሮጀክቱ ለህዝብ በተገለፀ ከአንድ ወር በሚያንስ ጊዜ ዉስጥ የግንባታዉ ስራ መጀመር ሚስጥራዊነት ግልፅነት የጎደለዉ ዕቅድ መሆኑ ለትችት እንዳጋለጠዉ ጠቅሷል። 

በድንገት የተገለፀዉ የግንባታ ስራ ግብፅ፤ የተፋሰሱን አገሮችና ሌሎችንም የሚመለከታቸዉን ሁሉ እንዳስደነገጠ በመግለፅ የውጭ ተቃዉሞን ላለመጫርና በተቃራኒዉ በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚያሳድረዉን ስሜት ከፍ ለማድረግ የታሰበ ሊሆን እንደሚችል ያለዉን ግምት አስፍሯል። 

የአቶ መለስን ንግግር ተከትሎ ስለ ግድቡ ስራ ማስታወቂያዎች፤ ፖስተሮች፤ ሪፖርቶች፤ መዥጎድጎዳቸዉን፤ የቦንድ ሽያጭ መጀመሩንና የአርበኝነት ስሜት ያደረባቸዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ የግድቡን ግንባታ ደግፈዉት እንደነበር  ዘገባዉ ገልጿ ል።

በዚህ ረገድ በተደረገዉ የተጠናከረ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ እስካለፈዉ መስከረም ወር ድረስ 7 ቢሊዮን ብር ወይንም 408 ሚሊዮን ዶላር መዋጣቱን ዘገባዉ ገልጾ ፣ ግብፅና ሱዳን እስካሁን ቅሬታ ባያሰሙም ወደፊት ግንኙነታቸዉ ሊሻክር ይችላል ብሎአል

የአባይ ግድብ ግንባታ መደናቀፍና አደጋ ሊገጥመዉ እንደሚችል በመጥቀስ በኢኮኖሚስት መረጃ መሰረት የኤሌክትሪክ ሃይሉን ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት አለመፈፀሙ አንድ ችግር መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የግንባታዉ ስራ  በአካባቢና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ ሊያስከትል የሚችለዉ የቴክኒክ ጥናት በመንግሰት አለመደረጉ የአለም ባንክንና ተመሳሳይ ተቋሞችን እንደሚያሳስባቸዉ ክርስቲያን ሳይንስ አብራርቷል።

ግንባታዉ ከተጀመረ ከ3 ወራት በሁዋላ አንድ የጣሊያን ኢንጂነር ቡድናቸዉ በግንባታ ስፍራዉ ላይ ያሉ የአለት ድንጋይ ንጣፎችን በማጥናት ላይ እንደሆነ ገልፀዉ የአለት ድንጋዩ ንጣፉ መኖር ስፍራዉ ለግንባታዉ ስራ ተስማሚ እንዳልሆነ መስክረዋል።

ጥፋት የሚያስከትሉ ግድቦች በአለም አቀፍ ወንዞች ላይ እንዳይሰሩ የሚሟገት ድርጅት ፕሮጀክቱ መጥፎ አለም አቀፍ ልምድ መከተሉን አስረድተዋል።

የስራ  ኮንትራት ጨረታ የሌለዉ፤ በሚስጥር የተያዘና፡ ለዉይይት እንዳይቀርብ አፈና የተደረገበት፤በዚህም የተሳሳተ እቅድ የተከተለ በመሆኑ ከመነሻዉ ችግር ያለበት ነዉ ሲሉ የአለም አቀፍ ድርጅቱ የአፍሪቃ ተሟጋች መናገራቸዉን ዘገባዉ ያስረዳል።

የቀድሞዉ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኬን ኦሃሺ በበኩላቸዉ በምኞት ላይ የተመረኮዙ የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፣ በዉጭ ብድርና ፋይናንስ መደገፍ የዕዳ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የገለፁ መሆኑን የክርስቲያን ሳይንስ ሞኒትር ዘገባ በማጠቃለያዉ ላይ ጠቅሷል።