የአሜሪካ ኢምባሲ ዜጎቹ ወደ ባህርዳር እንዳይጓዙ አስጠነቀቀ

ታኅሣሥ ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሁለት ቀናት በፊት በባህርዳር ግራንድ ሆቴል የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ዜጎቹ ወደ ባህርዳር እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል። የኢምባሲው ሰራተኞች ወደ ባህርዳር እንዳይጓዙም እገዳ ጥሏል። ኢምባሲው በመግለጫው ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ የሚያስከትለውን አደጋ እየተከታተለ በማስታወቅ ላይ መሆኑን ጠቅሷል።

በባህርዳር የደረሰውን ፍንዳታ በተመለከተ ገዢው ፓርቲ የሰጠው መግለጫ የለም። ይሁን እንጅ በከተማዋ ፍተሻ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በጥርጣሬ የተያዙ ወጣቶችና ድርጅቱ ሰራተኞቸ መኖራቸው ታውቋል።

ከፍንዳታው በፊት ሆቴሉ የሙዚቃ ዝግጅት ለማዘጋጀት መወሰኑን ተመልክቶ ፣ “በከተማው የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ ሙዚቃ ማዘጋጀት ትክክል አይደለም” የሚል  በፌስቡክ የተቃውሞ ቅስቀሳ ይካሄድ ነበር። በከተማው የሚገኙ ወጣቶች እንደሚሉት ሆቴሉ የብአዴን ከፍተኛ ሹሞች በእጃዙር የሚያስተዳድሩት ነው። የሙዚቃ ዝግጅቱ በክልሉ ሰላም ሰፍኗል የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።

በአማራ ክልል በሁሉም ከተሞች አሁንም ህዝቡ ወደ መደበኛ ህይወቱ መመለስ አልቻለም። ወታደራዊ እዙ በየጊዜው ወጣቶችን እየያዘ ማሰሩ እንዲሁም “ ጸጉረ ልውጦች ገብተዋል” በሚል ሰበብ የሚደረገው ፍተሻ ህዝቡን በእጅጉ እያማረረ ነው።

በሌላ በኩል በባህርዳር ወህኒ ቤት የተገደሉት 4 ወጣቶች ያስከሬን ምርምራ ሳይደረግላቸው እንዲቀበሩ ተደርጓል። በአዲስ ቅዳም ወረዳ በሚገኘው መሰናዶ ትምህርት ቤት ያስተምር የነበረው መምህር አሸናፊ ሸዋረጋው እና ሌሎች 3 እስረኞች ጠዋት ላይ ቁርስ በልተው ስፖርት በመስራት ላይ እያሉ ለየብቻ እየተጠሩ መርፌ መወጋታቸውን፣ ከዚህ በሁዋላ ሁሉም ህይወታቸውን ማለፉን ምንጮች ለኢሳት ገልጸው ነበር።

እስረኞቹ መሞታቸው ከታወቀ በሁዋላ፣ ፖሊሶች የእስረኞችን ቤተሰቦች ጠርተው እስረኞቹ በህመም እንደሞቱ ለማስረዳት ሞክረዋል። የእስረኛ ቤተሰቦች ግን አስቀድመው ከሌሎች እስረኞች ባገኙት መረጃ መሰረት እንዲሁም ሰዎቹ ስለመታመማቸው አንድም ቀን ሳይነገራቸው እንዲሁም አራቱም ተጥረተው ሲመለሱ መሞታቸውን በመጥቀስ ታመው ሞቱ የሚለውን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል። ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ቤተሰቦች ፣ ይህን አምናችሁ ማትቀበሉ ከሆነ በራሳችሁ ላይ ሌላ ችግር ትፈጥራላችሁ ተብለው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

የሟች መምህር አሸናፊ እናት ልጃቸውን እንዲያዩ ቢጠይቁም፣ አስከሬኑን አጅበው የሄዱት ፖሊሶች የልጃቸውን ፊት ብቻ እንዲያዩ በማድረግ ሌላውን የሰውነት ክፍሉ እንዳይከፈት አድርገዋል። አስከሬን ምርምራ እንዳይደረግ በማድረግ የቀብር ስነስርዓቱ ተፈጽሟል።

የመምህር አሻነፊ ጓደኞች ለኢሳት እንደገለጹት፣ መምህሩ ስለአገሩ የሚጨነቅና ለነጻነቱ ሲል ማንኛውንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነበር። በእስር ቤት ውስጥ እስረኞችን ታሳምጻለህ እየተባለ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ቆይቷል። የእሱን አሟሟት ለማጣራት ወደ ማረሚያ ቤቱ በሄዱበት ወቅት፣ በየጊዜው ተመሳሳይ ግድያዎች እንደሚፈጸሙ እንደነገሩዋቸው ተናግረዋል።

4ቱ ወጣቶች 7 ሆነው አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል ወደ በረሃ ሲሄዱ ከመካከላቸው አንደኛው ጠቁሙ አስይዟቸዋል። ጠቁዋሚው በአሁኑ ሰአት የመንግስት ስልጣን ተሰጥቶት በስራ ላይ ይገኛል።