የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮማንደሮችን ስራ መልቀቅ በተመለከተ ለኢሳት ዘገባ መልስ ሰጠ

ሰኔ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽኑ መልሱን የሰጠው ኢሳት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኪሚሽነር ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁና የምዕራብ ጎጃም ዞን የወንጀል ምርመራ ሃላፊ የነበሩት ኮማንደር በላይ ካሴ ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በማስመልከት ዘገባ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሽብር ማህበራዊ ሚዲያ አራማጆች የአማራ ክልል ኪሚሽን ስራ ባልደረባ የሆኑት ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁና ኮማንደር በላይ ካሴ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ለመቀጠል እንደሚቸገሩና እንደለቀቁ መዘገቡ የሃሰት ወሬ ነው ብሎአል። ይህን ይበል እንጅ ኮሚሽኑ ሁለቱም ሰዎች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ለመደበቅ አልቻለም።
ኮሚሽኑ “ኮማንደር አሰፋ የለቀቁት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሰብአዊ መብት ምርምራና ክትትል ዳይሬክቶሬት ሆነው በመሾማቸው ነው” ብሎአል። ኮማንደር አሰፋ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩበት ከነበረውና ቦታ ወርደው ስሙ ብዙም የማይታወቅ የአንድ ከተማ የሰብአዊ መብት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንዲሰሩ መደረጉ ፣ እንዴት ተሾሙ ሊባል እንደሚችል ፖሊስ በመግለጫው አላብራራም። የዜናው ምንጮች በፖሊስ የቀረበውን ማስተባበያ አሳፋሪ ብለውታል። የክልሉን ፖሊሶች በበላይነት ሲመራ የነበረው ሰው፣ ስራውን ከእንግዲህ አልፈልግም ብሎ ሲለቅና ዜናው በኢሳት ከተሰራጨ በሁዋላ፣ በአንድ ከተማ የሰብአዊ መብት ደርጅት ውስጥ እንዲወሸቅ አድርገው፣ “ሹመት ሰጠነው እንጅ ስራውን አልለቀቀም” በማለት ለመካድ መሞከራቸው ለህዝቡ ያላቸውን ንቀት ያሳያል ይላሉ።
ኮማንደር አሰፋ፣ በግምገማ ወቅት፣ “ዛሬ ላይ ማን ለማን እንደሚሰራ አይታወቅም” በማለት ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ መዘገቡ ይታወቃል። የክልሉን ፖሊሶች ለማረጋገት በሚል የተሰጠው መግለጫ፣ የክልሉ ፖሊሶች ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ በህወሃት ኮማንድ ፖስት ወድቋል በሚል ለሚያቀርቡት ትችት ተጨማሪ ማረጋገጫ የሚሰጥና እያሳዩት ያለውን ተቃውሞ ይበልጥ አጠናክረው እንዲገፉበት የሚያደርግ ነው ሲሉ የፖሊስ ምንጮቻችን ይናገራሉ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮምሽን የምዕራብ ጎጃም የወንጀል ምርምራ ሃላፊው ኮማንደር በላይ ካሴም ስራ መልቀቃቸውን አምኖ ስራ የለቀቁት ግን እርሳቸው ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረት ነው ብሎአል። ኮማንደሩ 25 ዓመታትን ያገለገልኩ በመሆኔና የጡረታ እድሜየም እየደረሰ በመሆኑ አሁን የያዝኩትን ሃላፊነት ለመወጣት ከብዶኛል በማለት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ምንም እንኳ ኮማንደር በላይ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ መሆናቸው እውነት ቢሆንም፣ የጡራ እድሜ ለመድረስ ገና የሚቀራቸው በመሆኑ፣ ችግር ባይኖርባቸው ኖሮ ጡረታቸውን አስከበርው መውጣት ይቀላቸው ነበር፤ ነገር ግን ስራው ከብዶኛል በማለት ከጡረታ መውጫ ጊዜያቸው 3 አመታት ያክል ቀድመው በቃኝ ማለታቸው ፣ በፖሊሶች ውስጥ የተነሳውን ተቃውሞ የሚያረጋገጥና የኢሳትን ዘገባ የሚያረጋገጥ እንጅ የሚያስተባብል አይሆንም ሲሉ ፖሊሶች ይገልጻሉ። ኢሳት አቅርቦት በነበረው ዘገባ “ ኮማንደር በላይ የኮሚሽነርነት ማእረግ ከመታለት በሁዋላ ፣ በባህርዳር በተካሄደው ግምገማ ይቅርብኝ አልፍለግም” በማለት ስራ መልቀቁን ገልጾ ነበር።
በርካታ ፖሊሶች የጡረታ እድሚያቸው ደርሶ እንኳን ወዲያውኑ እንደማይከበርላቸው የሚገልጹት ምንጮች፣ በተለይ ኮማንደር በላይ የኮሚሽነርነት ማእረግ በሚሰጠው ሰአት አልፈልግም በማለት መሰናበቱ የግለሰቡን ጥንካሬ ያሳያል በማለት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮማንደር በላይን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤን በማስረጃነት አያያዞ ያቀረበ ሲሆን፣ ደብዳቤው የተጻፈበት ጊዜ የኮማንድ ፖስት አባላት የአማራ ክልልን ፖሊሶችን መገምገማቸውን ኢሳት በዘገበበት በግንቦት ወር መሆኑ የኢሳትን መረጃ ትክክለኛነት ይበልጥ የሚያጠናክረው ነው። የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት የአቶ አለምነው መኮንን የግል አጃቢ መገደል ፣ በግምገማ ወቅት ስራችንን አንፈልግም በማለት ጥያቄ ላቀረቡ ፖሊሶች አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ማድረጉን ምንጮች ይገልጻሉ። የባህርዳሩ ግምገማ ከተካሄደ በሁዋላ በርካታ የፖሊስ አዛዦች ስራቸውን ለቀዋል። የቲሊሊ ከተማን ፖሊስ አዛዥ ጨምሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ፖሊሶችም ታስረዋል።
የክልሉ ፖሊሶች ዋና ተቃውሞ በህወሃት የሚመራው ኮማንድ ፖስት የክልሉን ፖሊሶች ከጨዋታ ውጭ አድርጎ በራሱ ጊዜ ያሻውን እርምጃ ይወስዳል የሚል ነው። አንዳንድ የፖሊስ አዛዦች ስልጣናቸው የይስሙላ መሆኑንና የክልሉን ጸጥታ ህወሃት መረከቡን ይገልጻሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህወሃትን የበላይነት ይቃወማሉ የሚባሉ ፖሊሶችን ለማባረር እንደጠቀመ የሚገልጹት ምንጮች፣ ህወሃት በክልሉ ውስጥ ያለውን የበላይነት አስጠብቆ ለመቆየት በታማኞቹ አማካኝነት ኔትወርክ መዘርጋቱንም ይገልጻሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደተጠናቀቀ በነባር የፖሊስ አዛዦችና በህወሃት ታማኝ ፖሊሶች መካከል፣ የስልጣን ይገባኛል ውዝግብ እንደሚነሳና አለመተማመኑም እንደሚጨምር፣ የፖሊሶቹ መከፋፈለም ህወሃትን እንደሚጠቅም እነዚሁ የፖሊስ ምንጮች ይገልጻሉ። አንዳንድ ፖሊሶች ይህንን ለማስቀረት የውስጥ ለውስጥ ንግግር መጀመራቸውንና ሌሎችም ፖሊሶች ለማንቃት እየተንቀሳቀወሱ መሆኑን ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ዜና በክልሉ የህወሃት አገልጋይ የሆኑ ባለስልጣናት የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸውና የግል ጥበቃቸው እንዲሻሻልላቸው ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጥያቄ አቅርበዋል። አስተማማኝ የደህንነት ጥበቃ ካልተደረገላቸው ስራቸውን ለመስራት መቸገራቸውንም እነዚህ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
በክልሉ ውስጥ ያለው የደህንነት ሰራተኞች መከፋፈል፣ በሚደረግላቸው ጥበቃ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው አድርጓል። አቶ አለምነው የግል አጃቢ ከውስጥ አርበኞች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ መገደሉ መረጃው ይፋ ከሆነ በሁዋላ፣ በርካታ የህወሃት ታማኝ ባላስልጣናት ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑን በመግለጽ ጥበቃው ይጠናከረልን ብለዋል።