የአማራ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ከስልጣን ተነሱ

ታኅሣሥ ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በክልሉ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ መቆጣጠር አልቻሉም በሚል የአስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ደሴ አሰሜ ከሃላፊነት ተነስተው እንዲንሳፈፉ ተደርጓል።

ለአገዛዙ ታማኝ ናቸው የሚባሉት አቶ ደሴ፣ እንደሌሎች ከሃላፊነት እንደተነሱት ሰዎች ወደ እስር ቤት ባይወሰዱም፣ በአሁኑ ሰአት ከስልጣን ተነስተው ያለስራ ተቀምጠዋል። በክልሉ ውስጥ በተለይም የሙስሊም አትዮጵያውያን እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት፣ በሙስሊሞች ላይ የሃይል እርምጃ እንዲወሰድ፣ እንዲሁም በክልሉ ወጣቶች ላይ ለሚፈጸሙ ተደጋጋሚ አፈናዎችና ግድያዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የክልሉ የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ። ከዚህ ቀደም በሚደረጉ ተደጋጋሚ የደህንነት ስብሰባዎች ውዳሴ ሲቀርብላቸው የቆዩት አቶ ደሴ ፣ በመጨረሻ የክልሉን ጸጥታ አልተቆጣጠሩም ተብለው እንዲነሱ መደረጋቸው አገዛዙን ለሚያገለግሉ ለሌሎች ባለስልጣኖችም ጥሩ ትምህርት የሰጠ ነው ሲሉ የዜናው ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ከጎንደር ለማውጣት በተደረገው እንቅስቃሴ ከኮሎኔሉ ጎን በመቆም በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲፈጠር እንዲሁም ኮሎኔሉ በእስር ቤት በልዩ ሁኔታ እንዲጠበቁና እንዲያዙ አድረገዋል በሚል የተያዙት የጎንደር ማረሚያ ቤት ሃላፊ የነበሩት ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረት አሁንም ጉዳያቸውን የሚመለከትላቸው ባለስልጣን አጥተው በእስር ላይ ይገኛሉ። በአመራር ድክመት በአገዛዙ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉት የዞኑ የጸረ ሽምቅ ሃላፊው ኮማንደር ዋኘው አዘዘም እንዲሁ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ክስም ሳይመሰረትባቸው ከኢንስፔክተር ልጃለም ጋር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ  ታስረዋል።

በቅርቡ ባህርዳር ከተማ ፓፒረስ ሆቴል ላይ ተደርጎ በነበረው የክልሉ የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ስብሰባ ላይ የኢንስፔክተሩ ጉዳይ ቢነሳም ፣ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ዘለቀ፣ ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል። ክልሉ ባለስልጣኖችን የመሾምም ሆነ የማውረድ ስልጣን ቢኖረውም፣ የክልሉ ክተኛ ባለስልጣናት ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ነው ማለታቸው፣ አማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን “ ኮማንድ ፖስት” ለሚባለው ወታደራዊ እዝ ማስረከቡን የሚያሳይ ነው ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል በሰሜን ወሎ ለሚገኙ አርሶአደር ወጣቶች ወታደራዊ ስልጠና መስጠቱ መቀጠሉን ምንጮች ገልጸዋል። ኢሳት በትናንት ሃሙስ ዘገባው ስልጠናው በዳውንት ወረዳ እንደሚሰጥ ዘግቦ የነበረ ቢሆንም፣ ስልጠናው ግን በሰሜን ጎንደር ባሉ ሁሉም ወረዳዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሰልጣኞች ፣  ከስልጠና በሁዋላ ወደ ሰሜን ጎንደር እየተላኩ ጥበቃ ያካሂዳሉ። አብዛኞቹ ሰልጣኞች የሚመለመሉት ምንም አይነት መረጃዎችን ከማያገኙ አካባቢዎች ነው።