የቦሌ መደበኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ጦማሪ አቤል ዋበላ ላይ ወደ መደበኛ ስራው እንዳይመለስ ሲል ፈረደ

ታኅሣሥ ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከዞን 9 ጦማሪዎች ጋር አንድ ዓመት ከአምስት ወራት በእስራት ያሳለፈውና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በቴክኒሻን መሃዲስነት ሙያ ሲያገለግል የነበረው ጦማሪ አቤል ዋበላ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ከእስር በነጻ ከተለቀቀ   በኋላ  በነጻ የተለቀቀበትን የፍርድ ቤት መረጃ በመያዝ ወደ መደበኛ ስራው ቢሄድም አየር መንገዱ ወደ ስራ ገበታው እንዳይመለስ እገዳ ጥሎበታል።

የአየር መንገዱን ውሳኔ በመቃወም አቤል ወደ ፍርድ ቤት ክስ ቢያቀርብም፣  አየር መንገዱ በበኩሉ “ለሰጠንህ ስልጠና ለሰባት ዓመታት ለማገልገል የፈረምከውን የኮንትራት ውል አላሟላህም” በማለት በተቀራኒው ክስ መሰርቶበታል። ፍርድ ቤቱም በአቤል ክስ ላይ ብይን  ሳይሰጥ ሁለተኛውን ክስ እንደማይቀበለው አስታውቋል ።

ጦማሪ አቤል ዋበላ የስራ ውሉን ያቋረጠው “በሕጋዊ መንገድ ነው? አይደለም?” የሚለውን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ሲይያ የቆየ ሲሆን ፣ የቦሌ መ/ደ/ፍ/ቤት ታኅሣሥ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት አየር መንገዱ “ከ30 ቀን በላይ ታስሮ የቀረበትን ሠራተኛ ወደ ሥራ ገበታው የመመለስ ግዴታ የለበትም”  በማለት  ፍርድ ቤቱ ለአየር መንገዱ ፈርዷል።

ከሕግ አግባብ ውጪ ለእስር የተዳረገው ጦማሪ አቤል ዋበላ ካለምንም ካሳ ቢፈታም ወደ መደበኛ ስራው እንደይመለስ መደረጉ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማዘኑን እና ተስፋ አስቆራጭ ስሜት እንደተሰማው ተናግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያደረሰበትን በደል በሚመለከት ለቀጣይ እስከመጨረሻው ድረስ በሕግ መጠየቁን እንደማያቋርጥ ጦማሪ አቤል ዋበላ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና እና በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ስራ ከሚሰራባቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑ ይገለጻል። ከአስተዳደር እስከ ፀጥታ ያሉ የስራ ቦታዎች  በአብዛሃኛው በህወሃት ሰዎች የተያዘ መሆኑን ሰራተኞች ይገልጻሉ።