የብሪታኒያ ሌበር ፓርቲ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ለሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ህዳር 20 ፥ 2009)

የብሪታኒያው አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለሃገሪቱ  ዜጎች መብት መከበር የገቡትን ቃል በማክበር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የሃገሪቱ ሌበር ፓርቲ ጥሪውን አቀረበ።

በአቶ አንዳርጋቸው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ መግለጫን ያወጣው ፓርቲው፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ ለማድረግ የፊርማ ድጋፍ የማሰባባሰቢያ ዘመቻ እንደሚያካሄዱም ይፋ አድርጓል።

ላለፉት ሶስት ወራት የብሪታኒያ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው እንዳይጎበኙ ተደርጎ መቆየቱን ያወሳው ሌበር ፓርቲ፣ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስቧል።

በቅርቡ የተሾሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቦሪስ ጆንሰን ስልጣናቸውን በተረከቡ ጊዜ የብሪታኒያ ዜጎች ጥቅም መከበር ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ የገቡትን ቃል በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው የፓርቲው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ለሶስት ወር ያህል ጊዜ በብሪታኒያ ተወካዮች እንዳይጎበኙ ጥሎት የሚገኘው እገዳ በብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ልዩ ትኩረት ስቦ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።

የብሪታኒያው ሌበር ፓርቲ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን አስመልክቶ ለሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ ስጋቱን እየገለጸ መሆኑንም አክሎ አስታውቋል።

የቀድሞው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊሊፕ ሃሞንድ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የህግ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ሁለቱ ወገኖች የደረሱት ስምምነት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሊደረግ አለመቻሉን የሌበር ፓርቲው በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰን ከተለያዩ አካላት እየቀረበ ያለውን ስጋት ግምት ውስጥ በማስገባት ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አፋጣኝ ምላሽን እንዲሰጥ ፓርቲው አክሎ አሳስቧል።

የብሪታኒያው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትና የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይን በመከታተል ላይ የሚገኘው ሪፕሪቭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ለደህንነታቸው ስጋት እንዳደረባቸው መግለጻቸውን በቅርቡ ይፋ ማደረጉ ይታወሳል። ይሁንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።