የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለሽያጭ መቅረቡ በድርጅቱ ሰራተኞች ላይ ስጋት አሳድሯል

ጥር ፭ (አምስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ 40 በመቶ ለሽያጭ መቅረቡን በተመለከተ ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ከዘገበ ወዲህ የድርጅቱ ሰራተኞች ”ድርጅቱ አትራፊ ሆኖ እያለ ለምን ለሽያጭ እንዲቀርብ ተደረገ?” በማለት ቅሬታ ማሰማት ጀምረዋል። ሰራተኞቹ ከስራ ገበታችን ልንነሳ እንችላለን የሚል ከፍተኛ  ስጋት  ላይም ወድቀዋል።

ድርጅቱ ለቻይና ኩባንያ ለሽያጭ ይቀርባል መባሉ በድርጅቱ ሰራተኞች  ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነ ሲሆን ፣ እ.ኤ.አ. 2016 የቻይና የመርከብ ድርጅቶች ኪሳራ ማስመዝገባቸው እየታወቀ ”እነሱ እየከሰሩ እንዴት እኛ ከነሱ ጋር እንሰራለን?” ”እንዴት ለቻይና ድርጅት ይሸጣል?” ሲሉ ሰራተኞች ይጠይቃሉ።

አራቱም ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ የባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት፣ የደረቅ ወደቦች ድርጅት በመጨረሻም ኮሜት አክሲዮን ማህበር በጋራ ተዋህደው መስራት ከጀመሩ ወዲህ አስተዳደራዊ በደሎች በመስሪያ ቤቱ ውስጥ እንደሚፈጸሙም ሰራተኞች ይናገራሉ። ሙያ ከሚጠይቁት የድርጅቱ የስራ መስኮች ውጪ አስተዳደራዊ ሹመቶች በድርጅታዊ አሰራር ተተክቷል። በሙያተኞች የተያዙት ሹመቶች ቀድሞ በኦህዴድ እና ብአዴን የድርጅት አባላቶች የተያዙ የነበረ ሲሆን አሁን ግን አንጋፋውን የስራ የሹመት ቦታዎች ህወሃቶች እየተቆጣጠሩት መጥተዋል። በድርጅቱ ተስፋ የቆረጡ ሰራተኞች መስሪያቤቱን በገፍ በመልቀቅ ላይ ሲሆኑ በምትኩ በብዛት የአዳዲስ ሰራተኞች ቅጥር እየተፈፀመ ነው። አዳዲስ የሚቀጠሩት ሰራተኞችም ድርጅቱን ከውጭ እንደገመቱት ስለማይሆን ጥቅም የለው እድገት የለው በሚል ምክንያት ጥለው ይሄዳሉ።

ድርጅቱ ዓለምአቀፍ ድርጅት ሆኖ እያለ ለካፒቴኖች የሚከፈለው ክፍያ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ካፒቴኖችም ስራቸውን ይለቃሉ። ከስራ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የአንድ ለአምስት አሰልቺ ፖለቲካዊ ግምገማም ለሰራተኞች መልቀቅ አንዱ ምክንያት መሆኑ ሰራተኞች ይገልጻሉ።

ለመርከብ ጥበቃ ከመከላከያ ሰራዊት የሚመደቡት አብዛኞቹ የህወሃት አባላት ሲሆኑ፣ ይህም ሆን ተብሎ በዶላር የሚከፈለውን ክፍያ እነሱ ብቻ  እንዲያገኙ እና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን ከሌላው የሰራዊቱ ተለይተው እንዲጠቀሙ ታስቦ መደረጉን የድርጅቱ ምንጮች ይናገራሉ። የባህር ትራንስፖርት ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዳሬክተር የሆኑት አቶ የኋላወርቅ የድርጅቱን ለሽያጭ መቅረብ አስመልክቶ ከ ጋዜጣ ላይ ከማንበባቸው ውጪ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ መመሪያ አለመውረዱን አስታውቀዋል። ጋዜጣው ያወጣው ”ትክክለኛ  መረጃ ነው?” ”አይደለም?” የሚለውን ለማወቅ አለመቻላቸውን እና የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ የልማት ድርጅቶች አስተዳደርም መረጃ እንደሌላቸውና ይህ ውሳኔ እውነተኛ ነውም አይደለምም ለማለት እንደሚቸገሩ ለኢሳት ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት 2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ ድርጅቱ 1.29 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማትረፉን ገልጿል።

ገዢው ፓርቲ በገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት  ወይም የቻይና ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ካለመክፈል የተነሳ በግዳጅ አትራፊውን ድርጅት ለመሸጥ ሳይገደድ አይቀርም በማለት ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።