የቀን ገቢ ግምት በማስላት በነጋዴዎች ላይ የሚጣለው ግብር ከፍተኛ ተቃውሞ አስከተለ

ሰኔ 14 ፥ 2009

የቀን ገቢ ግምትን በማስላት በነጋዴዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተቃውሞና ውጥረት ማስከተሉን የኢሣት ምንጮች ከአዲስ አበባ ገለፁ። በተለይ በዋናው የገበያ ማዕከል መርካቶ ነጋዴዎች እየተዋከቡ ሲሆን እርምጃው ነባር ነጋዴዎችን እየገፋ እዚህ መድረሱንም መረዳት ተችሏል።

ድንገት በገበያ ሥፍራዎች የሚሰማሩትና በኢሕአዴግ የተለያዩ መዋቅር የተሰለፉት የቀን ግምት ገማቾች ግዢ ፈፅመው የሚሄዱ ሸማቾችን ጭምር በማዋከብ ላይ መሆናቸውን የሚገልፁት የኢሣት ምንጮች ፌደራል ፖሊስም በማዋከቡ ሂደት ተሣታፊ መሆኑን ገልፀዋል።

በነጋዴዎቹ ሱቅ ውስጥ በመገኝት በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ በመተመን የግብር መጠን የሚወሥኑት እነዚህ ግለሰቦች በፓርቲ መዋቅር የሚታዘዙ በመሆናቸው ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸውንና በብሔረሰብም ለመጥቀም የሚፈልጉትን ቡድን መረጃ በመሥጠትና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በማድረስ ዕቃውን እንዲያሸሽ በማድረግ የግብር ተመኑን ዝቅ እንዲልለት እንደሚሰሩም ተመልክቷል።

በዚህ ድርጅታዊ መዋቅር ለመጉዳት በሚፈልጉት ነጋዴ ላይ 10 ሺህ ብርና ከዚያ በላይ የግብር ዋጋ ከወሠኑ ለድርጅት አባላትና በብሔረሠብ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሚፈለጉ በተለይም ለትግራይ ተወላጆች ዝቅ ያለ ከ500 ብር ያነሰ የዋጋ ተመን በመወሰን ሌሎችን እያከሰሩ ማስወጣት እንደግብ መያዛቸውን እኚሁ ምንጮች አብራርተዋል።

በዝቅተኛ ነጋዴዎች ላይ የተወሰነው የቀን ገቢ ግምት ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ነባር የሆኑ ነጋዴዎች እየተገፉ አዳዲስ ነጋዴዎች በሥፋት እየገቡ መሆናቸውም ታውቋል።

በዚህ የቀን ገቢ ግምት ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎች ቁጥር በሀገር አቀፍ ደረኛ 200 ሺህ ያህል ሲሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ከ150 ሺህ በላይ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።