የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለ2ተኛ ጊዜ ሕገመንግስቱን በመጣስ ተራዘመ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 8/2010) በኢትዮጵያ ዘንድሮ መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለ2ተኛ ጊዜ ሕገመንግስቱን በመጣስ መራዘሙ ተነገረ።

የሕዝብ ቆጠራው እንዲራዘም የተወሰነው በሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ነው ተብሏል።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የሕዝብ ቆጠራው እንዲራዘም የተፈለገው ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበት ሁኔታ ማካሄዱ ሌላ ቀውስ ይፈጥራል በሚል ነው።

ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት በህዳር 2010 ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበት ሁኔታ ማካሄድ እንደማይቻልና ህገ መንግስቱን መጣስ አማራጭ የሌለው መሆኑን የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑን የኢሳት የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

የአመቱን የመንግስትና የድርጅት እቅድ ለማውጣት በመቀሌ ተሰብስቦ የነበረው የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ብአዴን፣ኦህዴድና ደኢሕዴን ያቀረቡትን አስተያየት ከግምት በመውሰድ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዲራዘም መወሰኑ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የአመቱን የመንግስት ስራዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያቀርቡበት ሰአት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይ ትኩረት እንዳይሰጡ ትእዛዝ በመተላለፉ ህገ መንግስቱን ለመጣስ መገደዳቸው ተነግሯል።

የኢህአዴግ ህገ መንግስት አንቀጽ 103 ንኡስ አንቀጽ 5 የሕዝብ ቆጠራ በየአስር አመቱ ይካሄዳል ይላል።

የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘም ቢኖርበት እንኳን የሕገ መንግስት ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቅ በመሆኑ ይህ ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላ ቆጠራው መራዘሙ መንግስትን እንደሚያስጠይቀው ኢሳት ያናገራቸው የህግ ምሁራን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቀድሞ ፓርላማ አባል ለኢሳት እንደገለጹት ቆጠራው የተራዘመበት ምክንያት ከሙስናና ከሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለቆጠራው ያስፈልጋሉ ተብለው የተገዙት ከ180 ሺ በላይ ዲጂታል ታብሌቶችና ኮምፒዩተሮች ጋር ተያይዞ የተፈጸመው ሙስና እንዲሁም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገዙ ቁሶች ደብዛ መጥፋት ለመራዘሙ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በሀገር ውስጥ ለሚታተሙ ጋዜጦች ቆጠራው መራዘሙን አረጋግጠዋል።–ቆጠራው የተራዘመበትን ምክንያት ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

በህወሃት ኢህአዴግ ዘመን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ከምርጫ ክልል አወሳሰን፣ከበጀት ድጎማ፣ከሃይማኖትና ከብሔረሰቦች ማንነት እንዲሁም ከብዛት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የፖለቲካ ውሳኔ እንደሚያርፍበት ይገለጻል።

በቀጣይ የሚካሄደው ቆጠራ ላይ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መሪ ተዋናይ መሆኑ የቆጠራው ውጤት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚያርፍበት አመላካች መሆኑ ተገልጿል።