ክፍያ ቢፈጽሙም የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን የሙዚቃ አልበም እንዳይሸጡ መከልከላቸውን ነጋዴዎች ተናገሩ

ሚያዝያ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር እና ጎንደር ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች እንደገለጹት የዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ “ኢትዮጵያ” የሚለው አዲሱ የሙዚቃ ስራው በመኪኖች ላይ እየተዞረ እንዳይሸጥ ተከልክሏል። ነጋዴዎቹ “በአዲስ አበባ እንጅ በዚህ አካባቢ እንድትሸጡ ፈቃድ አልተሰጣችሁም” ከተባሉ በሁዋላ የማከፋፈል ፈቃድ ሲጠይቁ ከአንዱ መስሪያ ቤት ወደ ሌላው በማመላለስ ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።
የቅስቀሳ ስራ ለመስራት በቀን 500 ብር ክፍያ የሚፈጸም በመሆኑ፣ ይህንኑ ክፍያ ለአማራ ማስ ሚዲያ መክፈላቸውን የሚናገሩት ነጋዴዎች፣ በዚህ መሰረት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ለአንድ ቀን ተዛዙረው ሽያጭ ከፈጸሙ በሁዋላ እገዳ ደርሷቸዋል። ያም ሆኖ ግን የአርቲስቱ ስራዎች በተለያዩ ሱቆች በብዛት እየተሸጡ ነው።
የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አዲሱ የሙዚቃ ስራ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘ ከእያካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።