ከ70 ሺ በላይ የሚሆኑ የጋምቤላ ተወላጆች ያለፈቃዳቸው ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲነሱ ተደርጓል ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ክስ አቀረበ

ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-ታዋቂው የሰብአዊ መብቶች አቀንቃኝ ድርጅት “ሞትን እዚህ እየጠበቅን ነው፤ በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል ሰዎች በሀይል ከቦታቸው እየተፈናቀሉ በመስፈር ላይ ናቸው” በሚል ርእስ  ባወጣው መግለጫ የመለስ መንግስት ሰፈራ በሚባለው መርሀ ግብር ከ70 ሺ በላይ የጋምቤላ ተወላጆችን ከቀያቸው አፈናቅሎ፣ ምግብ፣ የእርሻ መሬት፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት በሌለበት ቦታ አስፍሯቸዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በሰፈራው አንሳተፍም ባሉት ሰዎች ላይ የሀይል እርምጃ ወስደውባቸዋል።

ሰፋሪዎች በግዳጅ ከቦታቸው እንዲፈናቀሉ በመደረጉ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በርካታ ህይወት ጠፍቷል፣ የምግብ አቅርቦት ተሟጧል፣ የጸጥታ ሀይሎችም ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝረውባቸዋል።

የሂውማን ራይትስ ወች የአውሮፓ ተወካይ የሆኑት ጃን ኢግላንድ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ሂውማን ራይትስ ወች መረጃውን ያጠናከረው በክልሉ ከሚገኙ ሰዎች ጋር በመነጋጋር መሆኑን ገልጠው፣ አሁን የተጀመረው ሰዎችን በሀይል ከቦታ የማፈናቀል ጉዳይ ሁኔታዎች ምቹ እስከሚሆኑ ድረስ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሰፈራ ፕሮግራሙ አላማ መሬት ለኢንቨስተሮች ለመስጠት ሳይሆን ነዋሪዎች የተሻለ ምቾች የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፈልግ ነው በማለት የሚያቀርበውን ማስተባበያ ሚስተር ኢግላንድ አይቀበሉትም። 

የውጭ አገር ለጋሽ አገሮች በተዘዋዋሪ መንገድ ይህን በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እንደሚያበረታቱ ሚ/ር ጃን ኢንግላንድ ገልጠዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ የቪኦኤ ዘጋቢ የሆነው ፒተር ሀይላይን ፣ የሂውማን ራይትስ ወች ተመራማሪ የሆኑትን ቤን ራውለንስን በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኦሞድ ኦባንግ በ1994 እና 95 ዓም በአኝዋክ ህዝብ ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ እጃቸው እንዳለበት ማመናቸው፣ ለበለጠ ምርመራ በር ይከፍታል።

ኦሞድ ኦባንግ በቅርቡ በአኝዋኮች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የምጠየቅ ከሆነ፣ ትእዛዙን የሰጠኝ መለስ ዜናዊም መጠየቅ አለበት በማለት የተናገረው የፓርቲው ሊቀመንበርነት ቦታቸውን እንዲያጡ፣ በሂደትም ከፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ሊያስነሳቸው እንደሚችል የጋምቤላ ምንጫችንን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

በጋምቤላ ከ7 አመት በፊት የጸጥታ ሀይሎች ባደረሱት ጭፍጫፋ ከ1500 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የአቶ መለስ መንግስት ጉዳዩን እርሳቸው በአቋቋሙት አጣሪ ኮሚቴ አስመርምረው ፣ የመከላከያ ሰራዊቱ ጥፋት አልፈጸመም ማለታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጅ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና እንደ ጄኖሳይድ ወች የመሳሰሉት ድርጅቶች የመለስ መንግስት በአለማቀፉ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ግፊት በመወትወት ላይ ናቸው።