ከግብር ጭማሪው ጋር በተያያዘ የተጀመረው ተቃውሞ በስራ ማቆም አድማና ፍቃድ በመመለስ ቀጥሏል

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 24/2009)ከግብር ጭማሪው ጋር በተያያዘ የተጀመረው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች በስራ ማቆም አድማና ፍቃድ በመመለስ መቀጠሉ ታወቀ።
በአዲስ አበባ የተቃውሞ ጥሪ በአንዳንድ አካባቢዎች ተበትኗል።ስለ ግብር የተጠራው ስብሰባም አጀንዳው በመቀየሩ ሕዝቡ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱ ተገልጿል።
በምስራቅ ጎጃም በደብረማርቆስ በተወሰኑ የንግድ ቦታዎች የስራ ማቆም አድማ ተደርጓል።ደብረወርቅ ካለፈው አርብ ጀምሮ በአድማ ላይ እንደሆነች የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በባህርዳር ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በጎንደር ዛሬ አንዳንድ ሱቆችና መደብሮች መዘጋታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በደቡብ ወሎ አጅባር በአድማው ሙሉ በሙሉ መሳተፏም ተገልጿል።
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘውና በሀገሪቱ በበርካታ ከተሞች እየተካሄደ ያለው አድማና ተቃውሞ በዚህ ሳምንትም መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል። በተለይም በምስራቅ ጎጃም ሌሎች ከተሞችን በመጨመር በመካሄድ ላይ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሸበል በረንታ ተጀምሮ ሞጣና ቢቸናን ያዳረሰው ደብረወርቅን ያስከተለው አድማ ደብረ ማርቆስንና ፍኖተ ሰላምን ቀላቅሎ ቀጥሏል። በባህርዳር በአንዳንድ ቦታዎች አድማ መምታቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ሰራዊቱን ያሰማራው መንግስት በየመጋጠሚያ መንገድና ዋና ዋና ጎዳናዎች መሳሪያ ያነገቱ ወታደሮች አድማውን ለማስቀረት ጥረት ማድረጉ ተገልጿል።
በአጠቃላይ በምስራቅ ጎጃም ሸበል በረንታ ሞጣ ቢቸና ደብረወርቅ ደብረማርቆስ በከፊልና በሙሉ አድማ ማድረጋቸው እየተግለጸ ነው። በደምበጫ ዛሬ አድማ በነጋዴዎች መመታቱ ታውቋል። ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነጋዴዎች በአድማው ባይሳተፉም እስከ ነገ እንዲቀላቀሉ ጥሪ ኣንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል። በደብረታቦር አብዛኛው የንግድ ቦታ ከእንቅስቃሴ ውጭ መሆናቸውን መረጃው አመልክቷል።
በደብረ ታቦር ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ታጣቂ ሀይል የተሰማራ ቢሆንም ይህ ዜና እስከተጠናቀቀበት ድረስ ሱቆችና መደብሮች እንደተዘጉ ናቸው። ብሁዎችን ያስደነቀውና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ዳግም በማንገስ የተካሄደውን ደማቅ ትዕይንት ህዝብ ያደረግችበትን 1ኛ ዓመት ዛሬ እያከበረች ባለችው ጎንደር ከተማ በተወሰነ መልኩ የአድማ እንቅስቃሴ መታየቱ ታውቋል። በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ጎንደርን በታጣቂ ሰራዊት በማጥለቅለቁ አድማውን አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ መቀላቀል እንዳልቻለ ከአካባቢው ያነጋገርናቸው ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ ሽዋሮቢት ባለፈው ሳምንት የጥሪ ወረቀት መበተኑን ተከትሎ በዛሬ ዕለት በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች አድማ መምታቱን በፎቶግራፍ በተደገፍ መልኩ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በሸዋሮቢት የተበተነው ወረቀት ከነጋዴዎች የአድማ ጥሪ ባሻገር አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው። በተያያዘ ዜና በወሎ በአጀበር ከተማ ቅዳሜ የተጀመረው የነጋዴዎች አድማ መቀጠሉ የታወቀ ሲሆን በኃይል ለማስከፈት በመንግስት ታጣቂዎች የተወሰደው እርምጃ ባለመሳካቱ በርካታ ሱቆች መታሸጋቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ነጋዴዎች ሥለግብር የተጠራው ስብሰባ አጀንዳው በመቀየሩ ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ታውቋል። በስብሰባው የተገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ለኢሳት እንደገለጹት በወረዳ 5 በተለምዶ ቻይና ግቢ የተጠራው ስብሰባ በግብር ጉዳይ ለመነጋገር ተብሎ የተጠራ ቢሆንም ስብሰባዎቹ አጀንዳው በመቀየራቸው የተቀጣው የነጋዴው ማህበረሰብ ስብሰባ ረግጦ በመውጣት ተቃውሞን ገልጿል።
በአማራ ክልል በባህርዳርና በሌሎች ከተሞች እስከ ሐምሌ 30 የተጣለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ትዕዛዝ የተላለፈ መሆኑም ታውቋል። እስከሚመጣው እሁድ ግብር ያልከፈለ ነጋዴ የንግድ ድርጅቱ ይታሸጋል ንግድ ፍቃዱ ይቀማል የሚል ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።