ከህወሃት መሪዎች ጋር በሽርክና የሚሰሩ የሌላ አካባቢ ተወላጅ ጥቂት ባለሃብቶች ከፍተኛ ብድር እየወሰዱ መሆናቸው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 1 ፥ 2009)

ለኤፈርትና ለትግራይ ተወላጆች ከሃገሪቱ ባንኮች ከፍተኛ ሃብት በብድር መውጣቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ ከህወሃት መሪዎች ጋር በሽርክና የሚሰሩ የሌላ አካባቢ ተወላጅ ጥቂት ባለሃብቶች በተመሳሳይ ከፍተኛ ብድር እየወሰዱ መሆናቸውን ምንጮች ገለጹ። በሌላ በኩል በንግዱ አለም በራሳቸው ጥረት ውጤታማ የሆኑት ሲገፉ መቆየታቸውና አሁንም በመገፋት ላይ መሆናቸውንም ኢሳት ያጠናከረው ማስረጃ ያስረዳል።

በተለይ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ ብድር በመውሰድ ዕዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሄዱ ከሚገለጽባቸው ውስጥ አንዱ አቶ ብዙአየሁ ታደለ የተባሉ ሲሆን፣ እኚህ ሰው ከአቶ አባይ ፀሃዬ ጋር የጥቅም ቁርኝት እንዳላቸውም ይጠቀሳል። በዚህም የፈጠሩት ሽርክና ድሬዳዋ ሲሚንቶን መክፈል የሚገባቸውን 30 በመቶ ሳይከፍሉ እንዲገዙ ከተደረገ በኋላ ለፋብሪካው ማስፋፊያ በሚል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተሰጣቸው ብድር 1.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ባለሃብቱ አሁንም ዕዳውን በመክፈል ላይ አለመሆናቸውም ተመልክቷል።……..

ሌላው ከህወሃት መሪዎች ጋር በፈጠሩት ቅርበትና ሽርክና ከፍተኛ ብድር ከኢትዮጵያ ህግ ባንክ የተለቀቀላቸው የቀድሞው ሰራዊት ባልደርባ አቶ በላይነህ ክንዴ ሲሆኑ፣ ከባንኩ በብድር የወሰዱት ገንዘብ 600 ሚሊዮን መድረሱን ምንጮች ገልጸዋል። የቅባት እህሎች ላኪና የብረታ ብረት አስመጪ የሆኑት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ ከህግ ውጭ በተደረገላቸው ልዩ ዕገዛና ድጋፍ ኢትዮጵያ ሆቴልን የገዙ ሲሆን፣ አካባቢውን አፍርሰው ህንጻ እንዲገነቡ ተፈቅዶላቸዋል። በአቶ በላይነህ ክንዴ ባለቤትነት በተያዘው ንብረት ውስጥ የህወሃት ሰዎች ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ የህወሃት ሰዎች የሌላው አካባቢ ተወላጆችም በንግዱ ውስጥ በንቃት ይሳተፉ ከሚል ማሳያነት እየተጠቀመባቸው ጉልህ ድርሻ መያዛቸው ተመልክቷል።

ሌላዋ ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር በፈጠሩት ቅርበትና ሽርክና ከባንኮቹ ከፍተኛ ብድር እየወሰዱ መሆናቸው የተገለፀው ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙ ሲሆኑ፣ ባህርዳር በሚገኘው ፒኮሎ አባይ ሆቴልና ጋምቤላ በሚገኘው ሌላ ሆቴላቸው ስም የወሰዱት ብድር 300 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የዚህን ዕዳ ክፍያም ሆነ ወለድ ባልከፈለበት ሁኔታ ውስጥ ተጨማሪ ብድር እንደተፈቀደላቸው ተመልክቷል።

ሌላው የዋሽንግተ ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩ ጋር በቅርበትና በሽርክና ይሰራሉ የሚባሉት አቶ ፈለቀ በቀለ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የወሰዱት ብድር 180 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ያልተከፈለ የወለድ መጠኑን ጨምሮ 211 ሚሊዮን ብር እንዳለባቸው ተመልክቷል። ባለሃብቱ አዲስ አበባ ከተማ ባምቢስ አካባቢ ኖክ ማደያ ፊትለፊት ያለውን የዝቋላ ህንጻ ባለቤት ሲሆኑ፣ በቅርቡ ከዚህ ህንጻ ጀርባ ያሰሩትን ሌላ ባለአስራ አንድ ፎቅ ህንጻ ለአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት IOM ማከራየታቸውም ተመልክቷል። ግለሰቡ ከኦህዴድ አመራር ከአቶ ግርማ ብሩ ባሻገር ከህወሃት ሰዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች ያስረዳሉ።

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች የህወሃት ንብረት በሆነው ኤፈርት እንዲሁም በበርካታ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በተለየ ሁኔታ ከባንኮቹ ያለምንም ዋስትና ለአንዳንዶቹ እስከ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር መፍቀዱን እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ።

የሌላ አካባቢ ተወላጆች ሆነው በባንኮቹ የተለያዩ ተጠቃሚ የሆኑት በጣት የሚቆጠሩ ከላይ የተመለከቱት ባለሃብቶችን ጨምሮ ጥቂቶች እንደሆኑም ይገልጻሉ። እነዚህም ጥቂት በንብረቶቹ ላይ የህወሃት ሰዎችን ባለድርሻ በማድረጋቸው ተጠቃሚ መሆናቸውንና አንዳንዶቹም በንብረቶቹ ላይ ያላቸው ድርሻ ከህወሃት ሰዎች ያነሰ መሆኑም ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል በራሳቸው ጥረት በንግዱ አለም ተሰማርተው በአመታት የጥረት ውጤት ስኬታማ የሆኑ ነጋዴዎች በተደረገባቸው ጫና ከንግዱ አለም መውጣት ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውን ጭምር እየከፈሉ መሆናቸውን የኢሳት ተባባሪዎች በአማራ ክልል ጉዳይ ብቻ በከፊል ካደረጉት ምርመራ መረዳት ተችሏል።

በዚህ ረገድ ተገፈተው ከንግዱ አለም ከወጡትና ከግዙፍ ቢዝነስ፣ ወደ ትንሽ ንግድ ከተወሰኑት ውጪ ግዙፍ የስታር ቢዝነስ ግሩፕ መስራቾች አቶ አበባው መሃሪና አቶ ምንውየለት አጥናፉ ተጠቃሽ ሆነዋል።

የቡሬ ባጉና የማዕድን ውሃ ባለቤት አቶ አለሙ ተሰማ በተመሳሳይ ከንግዱ አለም ከተገፉት ውስጥ ተጠቃሽ ሆነው ተገኝተዋል። በሆቴል ኢንቨስትመንት ውስጥ በቀዳሚነት ተሳትፈው በተደረገባቸው ጫና ንግዳቸው ከመታጎሉ ባሻገር ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ የባህርዳር ርሶርት ሆቴል ባለቤት አቶ መኮንን ገበየሁ እና የፓፒረስ ሆቴል ባለቤት አቶ ጠብቀው በላይ እንዲሁም የብሉናይል ሆቴል ባለቤት አቶ ደረጀ ተጠቃሽ ሆነው ተገኝተዋል።