ኢትዮጵያ ባለፈው የበጀት አመት ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ በእርዳታና በብድር መልክ ማግኘቷ ታወቀ

ጥቅምት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፈው የበጀት አመት አገሪቱ በእርዳታና በብድር መልክ 47 ቢሊዮን ብር ወይም ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች።

ከዚህ ውስጥ 28 ቢሊዮን ብር በእርዳታ መልክ ቀሪው ደግሞ በብድር መልክ የተገኘ ነው። ባለፈው አመትም አገሪቱ ካለባት እዳ ውሰጥ  324 ሚሊዮን ብር እንደተሰረዘላት ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አገሪቱ ያለባትን እዳ በትክክት ለህዝብ ግልጽ አያውቅም። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአቶ መለስ አገዛዝ ወቅት ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቅ ገንዘብ ተበድራለች፡፡ ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ አምና ባወጣው ዘገባ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ በሙስና እና በተለያዩ መንገዶች ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገራት ባንኮች ተሻግሯል።

ኢትዮጵያ ላለፉት 20 አመታት ከ40 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ600 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ በእርዳታ እና በብድር መልክ ብታገኝም፣ የአብዛኛው ህብረተሰብ ህይወት ግን አሁንም ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።