አፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በሶስት ቀን ጊዜ መኖሪያ ቤታቸውን ልቀቁ ተባሉ

ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚኖሩ ከአንድ ሺ በላይ ነዋሪዎች ያለምንም ቅድመ ዝግጅት በሶስት ቀን ውስጥ ልቀቁ ተብለናል ሲሉ ቅሬታን አቀረቡ።

በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 በተለምዶ ፈለገ ዮርዳኖስ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የአፍሪካንና ቻይና የጋራ አለም አቀፍ ዘርፈ ብዙ ተቋማትና ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት እቅድ መያዙ ታውቋል።

ለዚሁ ግንባታ ሲባል 1ሺ 516 ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ የከተማው አስተዳደር ማስተላለፉን ከሃገሪ ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ይሁንና ከአካባቢው በሶስት ቀናቶች ውስጥ እንድንነሳ ተጠይቀናል የሚሉት ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዳልተሰጣቸውና በምትኩ የተሰጣቸው ቤቶች መሰረተ ልማት ያልተሟላለት እንደሆነ ቅሬታን አቅርበዋል።

ከዚህ  በተጨማሪ በቤተሰባቸው ግቢ ውስጥ ሌላ ቤት ሰርተው የነበሩና በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ምንም አይነት አማራጭ ሳይቀርብላቸው እንዲነሱ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ጸሃዬ መጋቢት 16 ቀን 2009 አም ጀምሮ ቤቶቹ መፍረስ እንደሚጀምር የካቲት 25 ፣ 2009 ከነዋሪዎች ተወካዮች ጋር ስምምነት መደረሱን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ለነዋሪዎቹ የተሰጣቸው ቤቶች መሰረተ ልማት እስኪሟሉላቸው ድረስ ለችግር እንዳይጋለጡ ተከራይተው እንዲኖሩ ገንዘብ መሰጠቱንም ሃላፊው ተናግረዋል።

ይሁንና አቶ ተወልደ ቦታው በአስቸኳይ በመፈለጉ ለተነሺዎች በቂ ጊዜ እንዳልተሰጣቸው አረጋግጠዋል። ነዋሪዎቹ በበኩላቸው በሶስት ቀናቶች ውስጥ የመኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመሄድ እንደማይችሉና የከተማው አስተዳደር ቅሬታቸውን በአግባቡ እንዲመለከተው ጠይቀዋል።

በከተማዋ ለልማት ተብለው የሚነሱ በርካታ ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር በቂ ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያን እንደሚሰጣቸው ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ በከተማዋ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋ ዳግም ሊከሰት ይችላል በሚል ከአካባቢው እንዲነሱ የተጠየቁ ነዋሪዎች ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ልቀቁ መባላቸው አግባብ አለመሆኑን ለኢሳት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባለሃብቶች እየቀረበ ያለን የቦታ ጥያቄ ለማስተናገድ በርካታ የመኖሪያ አካባቢዎችን ለመልሶ ማልማት ፕሮጄክት መካለሉ ታውቋል።

ተነሺ ነዋሪዎች በበኩላቸው የከተማው አስተዳደር ያለበቂ ዝግጅትና የተሟላ መሰረተ-ልማት የሌለው ስፍራን በመምረጥ እንዲነሱ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ባለፈው አመት በላፍቶ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ህገወጥ የተባሉ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ የተካሄደ ዘመቻ ግጭትን ቀስቅሶ ከ10 በላይ ሰዎች እንዲሁም አንድ የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ መሞታቸው ይታወሳል።