አሜሪካ አልሸባብ ላይ ልታካሄድ ባቀደቸው አዲስ ወታደራዊ ጥቃት ዙሪያ ላይ ለመምከር የመከላከያ ሚኒስትሯ ወደጅቡቲ ላከች

ኢሳት (ሚያዚያ 16 ፥ 2009)

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ጂም ማቲስ ሃገራቸው በሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ላይ ልታካሄድ ባቀደቸው አዲስ ወታደራዊ ጥቃት ዙሪያ ላይ ለመምከር ትላንት ዕሁድ በጅቡቲ ጉብኝት አደረጉ።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በአል-ሸባብ ታጣቂ ሃይል ላይ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያካሄድ በሃገሪቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ትዕዛዝ ከተሰጠው በኋላ የመከላከያ ሚኒስትሩ በጅቡቲ ጉብኝት ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ማቲስ ሃገራቸው በአፍሪካ በብቸኝነት ያቋቋያመችውን ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ከጎበኙ በኋላ ከጅቡቲው ፕሬዚደንት ኢስማዔል ኦማር ጉሌህ እንዲሁም ከሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር አሊ ሃሰን ባህደን ጋር መምከራቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘግበዋል።

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሃገራቸው ጂኦግራፊያዊ ጠቅሜታ ባላት ጅቡቲ ያቋቋመችው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ በአፍሪካ ልምምዶችንና ተልዕኮዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጠቅሜታ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ይሁንና በቅርቡ ቻይና በጅቡቲ ተመሳሳይ ወታደራዊ ጣቢያ ከማቋቋም የያዘቸው ዕቅድ ከወታደራዊ ተልዕኮ አንጻር ስጋት ማሳደሩን ወታደራዊ ባለስልጣናት ማሳወቃቸውን ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።

የሃገሪቱ የአፍሪካ ወታደራዊ ሃላፊ የሆኑት ጀኔራል ቶማስ ዋልድሃሰር ቻይና በጅቡቲ የምታቋቁመው ወታደራዊ ጣቢያ በየትኛውም ስፍራ ካለ ወታደራዊ ጣቢያ እጅጉን የተቀራረበ መሆኑን አስረድተዋል።

ይኸው ያልተለመደ ነው የተባለው የማዘዣ ጣቢያው መቀራረብ የደህንነት ስጋት እንደሚኖረው ወታደራዊ ባለስልጣኑ አክለው ገልጸዋል።

ከአሜሪካና የፈረንሳይ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎች በተጨማሪ 10 ሃገራት በጅቡቲ ተመሳሳይ ይዞታ ያላቸው ሲሆን፣ ሃገሪቱ ያላት ጂኦግራፊያዊ ጠቀሜታ የተለያዩ ሃገራትን ፍላጎት እየሳበ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስታውቀዋል።

የሃገራትን ስም ከመጥቀስ የተቆጠቡት የአሜሪካው መካላከያ ሚኒስትር ጀኔራል ማቲስ በጅቡቲ  ወታደራዊ ጣቢያን እያቋቋሙ ያሉ ሃገራት በአለም አቀፍ የውሃ ህጎች ተገዢ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል። አሜሪካ በአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ ለማካሄድ ላቀደቸው አዲስ ወታደራዊ ጥቃት በጅቡቲ የሚገኘውን ወታደራዊ ጣቢያ ለመጠቀም እቅድ እንዳላት ይነገራል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ለሃገራቸው መከላከያ ሚኒስቴር በሰጡት ትዕዛዝ በአልሸባብ ላይ የአየር ጥቃትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ወስነዋል።

ይህንኑ ወታደራዊ ዘመቻ ለማጠናከር ጄኔራል ማቲስ ከቀናት በፊት በግብፅ ጉብኝት በማድረግ ሽብረተኝነት በጋራ መዋጋት በሚቻልበት ዙሪያ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መምከራቸው ይታወሳል።