ብሪታኒያ ለአፍሪካ አገራት የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ለሚደረግ እቅድ ማስፈጸሚያነት እንዲውል ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት (የካቲት 14 ፥ 2009)

የብሪታኒያ መንግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተወሰኑ የአፍሪካ ሃገራት የሚሰጠውን አመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት እያካሄደ ላለው እቅድ ማስፈጸሚያ እንዲያውለው የሃገሪቱ ሚኒስትሮች ጥያቄን አቅረቡ።

ለአፍሪካ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲታጠፍ ጥያቄን እያቀረቡ ያሉ የብሪታኒያ ሚኒስትሮች ሃገራቸው ድጋፍን በምስራቅ አውሮፓ ከሚገኙት ፖላንድ፣ ሃንጋሪ እና የባልቲክ ሃገራት (ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያና፣ ሊቶኒያ) ድጋፍ እንዲውል ጥያቄን አቅርበዋል።

የብሪታኒያ መንግስት በየአመቱ 12 ቢሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ አካባቢ የሚጠጋን ገንዘብ ለተለያዩ ሃገራት ድጋፍ የሚመደብ ሲሆን፣ አብዛኛው ገንዘብ ለአፍሪካ የሚመደብ መሆኑ ታውቋል።

በአፍሪካ ከዚሁ የገንዘብ ልገሳ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዘው ኢትዮጵያ ስትሆን፣ ደቡብ ሱዳንና ሴራሊዮን በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሶሪያ ደግሞ ከአፍሪካ ሃገራት በመቀጠል የብሪታኒያን ድጋፍ ከሚያገኙ ግንባር ቀደም ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

ሃገሪቱ ለአፍሪካ የምትሰጠውን ይህንኑ ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት እያካሄደች ላለው እቅድ እንዲሁም ዳግም ከህብረቱ ጋር ለምታደርጋቸው የተለያዩ ድርድሮች እንድትጠቀመው ሚኒስትሮቹ መጠየቃቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የብሪታኒያ ሚኒስትሮች የሃገሪቱ የልማት ድጋፍ በተለይ ጥያቄን ካስነሱ ሃገራት እንዲታጠፍ ትኩረትን የሰጡ ሲሆን፣ ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ተቃውሞ ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።

ባለፈው ወር ከሃገሪቱ የፓርላማ አባላት እና መገናኛ ብዙሃን ዘንድ የቀረበን ቅሬታ ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት የማህበራዊ ትምህርቶችን ለማስፋፋት ሲሰጥ የቆየው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቀር ማድረጉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴለቪዥን ስር ሊተላለፍ ለነበሩ ትምህርታዊ የሙዚቃና ድራማ ስራዎች ሊሰጥ ተወስኖ የነበረ የ5.2 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ የተቋረጠ ሲሆን፣ የኛ በሚል መጠሪያ የሚታወቁ የሙዚቃ ቡድን አባላት የቴሌቪዥን የራዲዮ ስራዎቹን አቅራቢ መሆናቸው ታውቋል።

የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ሃገሪቱ በተለይ ዜጋዋ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለእስር ተደርገው ባለበት ወቅት ለኢትዮጵያ የልማት እና ትብብር ድጋፍ ማድረግ የለባትም ሲሉ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ ለጤናና ለትምህርት ሲሰጥ የነበረው ድጋፍ በጋምቤላ ክልል ለመሬት ቅርምት ዉሏል የሚለውን ጥናት ተከትሎ ሃገሪቱ ለዘርፉ ስትሰጥ የቆየውን ድጋፍ ማቋረጧም የሚታወስ ነው።

የብሪታኒያው አለም አቀፍ የልማት ትብብር በበኩሉ በተወሰኑ የሃገሪቱ ሚኒስትሮች ዘንድ የቀረበው ሃሳብ ህገወጥ አካሄድ ሊሆን ይችላል በሚል ሃሳቡን እንደተቃወመው ሃፊንግተን ፖስት የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

የብሪታኒያ ሚኒስትሮች ሃገራቸው በምትሰጠው የልማት ድጋፍ ዙሪያ ጥያቄ የሚነሱባቸው ተለይተው የገንዘብ ድጋፍ ለሌላ አላማ እንዲውል ግፊት እያደረጉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ይኸው ሃሳብ በቀጣይ ሰፊ ክርክር ተካሄዶበት ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።