በጋምቤላ ክልል ከመከላከያ ሰራዊት በተተኮሰ ጥይት 3 ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ደግሞ ቆሰሉ

ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ ክልል ፉኝዶ ከተማ የመከላከያ ማዘዢያ ጣቢያ ውስጥ በድንገት በተተኮሰ ጥይት ሶስት ሰዎች ተገድለው ሁለት መቁሰላቸውን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ገልጧል።

ጥር 19 ፣ 2004 ዓም ከሌሊቱ 8 ሰአት ሲሆን  ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ታይተዋል ተብሎ፣ ሰራዊቱ በየአቅጣጫው በከፈተው ተኩስ የግለሰቦቹ ህይወት አልፎአል

በክልሉ የሚታየውን የመሬት ነጠቃ በመቃወም በርካታ ነዋሪዎች ነፍጥ እያነሱ የመከላከል እርምጃ እየወሰዱ መሆኑንም ንቅናቄው ገልጧል።

አሁን ተፈጠረ በተባለው ድንገተኛ ተኩስ አንድ እናት ወዲያውኑ ሲሞቱ ታዳጊ ልጃቸው ደግሞ ቆስላ በህክምና ላይ ትገኛለች። እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ የቆሰለ አንድ ጎልማሳ ህይወቱ አልፎአል።

ምንም እንኳ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ገብተዋል የተባሉት ሰዎች ባይገኙም፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግን አሰሳ በማካሄድ ላይ ናቸው።

በጋምቤላ ውስጥ ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ ውጥረት መስፈሩንም ንቅናቄው አክሎ ገልጧል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት የለም።