በከተሞች ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተተኪ ቦታ ባለማግኘታቸው እየተንገላቱ መሆኑን ተናገሩ፡፡

ሚያዝያ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመርአዊ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እንደገለጹት ፣ በተለያዩ ሰበቦች የእርሻ መሬታቸውን ከተነጠቁ በኋላ፣ ተተኪ የመኖሪያ ቦታ ባለማግኘታቸው ቤተሰቦቻቸው በቤት ኪራይ እየተሰቃዩ ነው።
ወይዘሮ ፈንታነሽ አድማሴ በመርዓዊ ዙሪያ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚኖሩበት አካባቢና የእርሻ ቦታቸው በመካለሉ አሮጌ ቤታቸውን አድሰው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ለመኖር ተከልክለዋል፡፡የከተማ አስተዳደሩ በእርጅና ምክንያት የፈረሰውን ቤት በማደስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመኖር ያቀረቡትን ጥያቄ አልተቀበለውም፡፡ቦታው ወደ ከተማ አስተዳደሩ በመግባቱ ምንም ዓይነት ግንባታ ማካሄድ አትችሉም በመባላቸው ለአቅመ አዳም የደረሱ ልጆቻቸው ከተማ ውስጥ ቤት ተከራይተው ለማኖር ተገደዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለሶስት ዓመት እንዳንገላታቸው የተናገሩት ወይዘሮ ፈንታነሽ “ልጆቼ በክራይ ቤት ተሰቃዩ” በማለት አቤቱታቸውን ያሰማሉ፡፡
ተለዋጭ ቦታ የሚሰጠን ከሆነ በቶሎ ይሰጠንና ሰርተን ቤተሰቦቻችንን እናስተዳደር ቢሉም፣ የመንግስት አመረራሮች ግን የመሬት ካሳውንም ሆነ ተተኪ ቦታውን ባለመስጠታቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ፡፡የገበሬ ማህበር አመራሮች አይመለከተንም የሚል ምላሽ በመስጠት ወደ ከተማ አስተዳደሩ ይገፋሉ፡፡የከተማ አስተዳደሩም ወደ ክልል በመግፋት እንግልት እንዳደረሱባቸወ በምሬት ይናገራሉ፡፡
በርካታ ባህር ዛፍ ቢኖረንም መጠቀም አልቻልንም የሚሉት ሌላዋ አቤቱቱ አቅራቢ፣ “አርሶ አደሮች እቅመ ደካሞችና በሽተኞች ብንሆንም እንደዜጋ ልንስተናገድ አልቻልንም” በማለት በምሬት ይናገራሉ፡፡”መርዝ ጠጥተን እንሙት ወይ?”በማለት የሚጠይቁት ቅሬታ አቅራቢዎች ይሄን ያህል ከምታሰቃዩን በመኪና ገጭታችሁ ብትገሉን ይቀለናል በማለት በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሚሰጣቸው ምላሽ፣ “ ከክልል ምላሽ አልተሰጠንም ነገ ተመለሱ ፣ሳምንት ተመለሱ “ የሚል በመሆኑ ከነቤተሰቦቻቸው እየተሰቃዩ መሆኑን በምሬት ገልጸዋል፡፡