70 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት እንደማያገኙ ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ህዝብ መካከል እስከ 70 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት እንደማያገኝ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ። 

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለማስፋፋት መንግስት እየመደበ ያለው አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ በጀት እቅዱን ለማሳካት እንዳላስቻለው የሚኒስቴሩን የ10 ወራት ሪፖርት ለፓርላማ ያቀረቡት ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ መግለጻቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።

“ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ህዝብ በገጠር በጨለማ ውስጥ እየኖረ መንግስት በሚመደበው አንድ ቢሊዮን ብር የትም ርቀት መሄድ አይቻልም” ሲሉ አቶ ስለሺ አስረድተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ከፍተኛ በጀት መመደብ ይኖርበታል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተያዘው በጀት አመት እንዲከናወኑ እቅድ የተያዘላቸው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ፕሮጄክቶች በእቅድ መሰረት ማከናወን እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርቱ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት የበርካታ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ስራ መስተጓጎሉን ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

በኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ካጋጠመው የበጀት እጥረት በተጨማሪ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት ተይዞ የነበረው እቅድም ተመሳሳይ የፋይናንስ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ሲገልፅ ቆይቷል።

የአለም ባንክና ሌሎች የፋይንናንስ ተቋማት መንግስት እየጨመረ ያለውን የብድር እዳ ክምችት ግምት ውስጥ በመክተት በብድር ፖሊሲው ላይ ማስተካከያ እንዲወሰድ አሳስቧል።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከኤሌክትሪክ ዘርፉ ባሻገር በአጠቃላይ በውሃ ኢንቨስትመንት ላይ የበጀት እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።