በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱንና የሃገሪቱም የውጭ ንግድ እያሽቆለቆለ መገኘቱን የንግድ ሚኒስትሩ ገለጹ። የመንግስት ባለስልጣናት ከፍተኛ የስልጣን መዋቅር እስከታችኛው ዕርከን በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ተዋናይ መሆናቸውም ከንግድ ሚኒስትሩ መግለጫ መረዳት ተችሏል።

በሳምንቱ አጋማሽ የመስሪያ ቤታቸው የ11 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ማክሰኞ ዕለት ለፓርላማ ያቀርቡት አዲሱ የንግድ ሚኒስትር ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ችግሩ ስር የሰደደ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እንደማይፈታ ማመልከታቸውን አዲስ አበባ ከሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ መረዳት ተችሏል።

ኮንትሮባንድ ሃገሪቱን እየገዘገዛት ነው በማለት ማብራሪያ የሰጡት አዲሱ ተሿሚ ሚኒስትር የመንግስት ባለስልጣናት በዚሁ ረገድ የሚሰጡትን መግለጫ ከመድረክ ፍጆታ ባሻገር በተግባር እንዲያውሉለትም ጠይቀዋል። “ድራማው መቆም አለበት ፥ የምንለውን ሆነን መገኘት አለብን” ሲሉም የችግሩን ስፋትና የመንግስት ባለስልጣናት በችግሩ ውስጥ ያላቸው ድርሻ አመልክተዋል።

በኮንትሮባንድ ወይንም በህገወጥ መንገድ ከሃገር በመውጣት በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡ ወርቅ እና የቁም እንስሳት መሆናቸውን ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚህ በኮንትሮባንድና በሌሎች ተፅዕኖዎች የሃገሪቱ የውጭ ንግድ አሁንም ከእቅዱ በታች ዝቅ ብሎ መገኘቱን የንግድ ሚኒስትሩ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ገልጸዋል። ባለፉት 11 ወራት ከውጭ ንግድ ለማግኘት የታቀደው 4.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የተገኘው ከዕቅዱ 59 በመቶ ቀንሶ 2.53 ቢሊዮን ዶላር መሆኑም አመልክተዋል። ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ2.53 በመቶ ቀንሶ መገኘቱንም ተመልክቷል።