በኢትዮጵያ የነዳጅ እጥረት ተባባሰ      

በኢትዮጵያ የነዳጅ እጥረት ተባባሰ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 21/2009) በኢትዮጵያ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው መሆኑ ተገለጸ።

በመላ ሀገሪቱ በተለይም በዋና ዋና ከተሞች የተከሰተው የነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በመገደቡ የምግብ እህሎች፣ሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች ምርቶች አቅርቦት ቀንሷል።

የዋጋ መናር መከሰቱንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ፣ባህርዳር፣ ደሴ ፣ደብረታቦር፣ደብረብርሃንና ደብረማርቆስ ተዟዙረው የገበያ ቦታዎችንና የነዳጅ ማደያዎችን የተመለከቱት ምንጮቻችን በማደያ ቦታዎች የሚታዩት መጨናነቆችና ረጃጅም ሰልፎች፣ታክሲዎችና ባጃጆች ነዳጅ ለማግኘት አለመቻላቸው የትራንስፖርት ችግሮች መባባሳቸውን ያሳያል ብለዋል።

በተለይም በሁሉም የነዳጅ ማደያዎች የነጭ ጋዝ አለመኖር ምግብ አብስሎ ለመብላት የማይቻልበት ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ያመኑት የማእድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ከችግሮቹ ዋነኛው የጅቡቲ ወደብ የገቢ እቃዎችን በበቂ ማስተናገድ አለመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የጅቡቲን ወደብ የኢትዮጵያ መንግስት ሊቆጣጠረው የሚችለው አይደለም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

በአመት ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ለነዳጅ ወጪ የምታደርገው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር በመሆኗና  40 በመቶ የቤንዝን አቅርቦቷን በሱዳን ላይ ጥገኛ ማድርጓ የችግሩን ቀጣይነት እንደሚያመላክት ምንጮቻችን ገልጸዋል።