በኢትዮጵያ በምግብ አለመመጣጠን ችግር የተነሳ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 53 በመቶ ሕጻናት እንደሚሞቱ ተነገረ፡፡

መጋቢት ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 23 በመቶ የሚደርሱ እናቶች የደም ማነስ ችግር እንዳለባቸውና ይህም ችግር በወሊድ ወቅት እስከሞት ለሚደርስ አደጋ እየዳረጋቸው መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ በምግብ አለመጣጠን ሳቢያ ገና በእናታቸው ማህጸን እያሉ ጀምሮ በህጻናት ላይ የጤና ችግሮች ሊከሰት እንደሚችል ይናገራል፡፡ ከጤና ችግሮቹ መካከል የሕጻናት ሞት፣ በተደጋጋሚ በበሽታ መጠቃት እና ከታመሙ በሁዋላ በቶሎ ማገገም አለመቻል፣ የሕጻናት ዕድገት መዛባት(መቀንጨር እና መቀጨጭ)፣ ከክብደታቸው ወይም ከተቀመጠው መስፈርት በታች የልጆች መወለድ፣ ያልተጠበቀ ውርጃ፣ የአእምሮ ዘገምተኝነትና የማየት ችግሮች ናቸው፡፡
ከእርግዝና ጀምሮ ሕጻኑ ተወልዶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ያሉት የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ወሳኝ መሆናቸው የታወቀ ነው የሚለው መረጃው፣ ይህ ጊዜ በተለይ በኢትዮጵያ በርካታ እናቶችና ሕጻናት ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚጎዱበት ነው ብሏል፡፡
የመቀንጨር ችግር የሚጀምረው በእርግዝና ወቅት በእናትየው ማህጸን መሆኑን ችግሩም አንድ ጊዜ ካጋጠመ የማይቀለበስ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜው ድረስ የመቀንጨር አደጋ የገጠመው ሕጻን ከቁመቱ 11 ሴንቲሜትር እንደሚያጥር፣ ካደገም በሃላ በትምህርት አቀባበሉ ደካማ እንደሚሆን፣ በሥራ ዓለምም ምርታማነቱ ስለሚቀንስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 67 በመቶ ያህሉ በልጅነቱ የመቀንጨር አደጋ ያጋጠመው መሆኑን በጥናት መረጋገጡን የጤና ጥበቃ መረጃ ያሳያል፡፡
ኮስት ኦፍ ሀንገር የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በአንድ ወቅት ባደረገው ጥናት መሰረት ኢትዮጵያን የምግብ አለመመጣጠን ችግር 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወይንም 16 ነጥብ 5 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት እንደሚያሳጣት አረጋግጧል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 የምግብ አለመመጣጠን ችግርን ወይንም መቀንጨርን ወደ 10 በመቶ፣ከመስፈርት በታች ክብደትን ወደ 5 በመቶ መቀነስ ከቻለች ፣ በዓመት 148 ቢሊየን ብር ማዳን ትችላለች፡፡ በግማሽ መቀነስ ከቻለች ደግሞ ወደ 71 ቢሊየን ብር ማዳን እንደምትችል አስቀምጦአል፡፡
ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት በመቀነስ በኩል ጥሩ ውጤት እንዳመጣች በተደጋጋሚ በገዢው ፓርቲ በኩል ሲገለጽ ቢቆይም፣ መረጃዎች የሚያሳዩት ግን አሁንም ከ5 አመት በታች ህይወታቸው የሚያልፍ ህጻናት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው።
የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ በሁዋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትና አሁን ለአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተርነት የሚወዳደሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የህጻናትና የእናቶችን ሞት በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ስራዎችን እንደሰሩ በመግለጽ የምረጡኝ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው።