በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተፈናቀሉት የኦሮሞ አርሶአደሮች ውስጥ 70 በመቶው ከመፈናቀላቸው በፊት ከነበረው በባሰ የኑሮ ጉስቁልና ውስጥ እንደሚገኙ ታወቀ

የካቲት ፲፬ ( አሥራ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር ባስጠናው ጥናት በአዲስ አበባና ዙሪያ ከተሞች ከተፈናቀሉ የኦሮሞ አርሶደሮች መካከል በተሻለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ የተባሉት 6 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ 70 በመቶ ያህሉ ግን ከመፈናቀላቸው በፊት ከነበራቸው የኑሮ ደረጃ ባሽቆለቆለ ኑሮ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በኦሮምያ ለተነሳው ተቃውሞ መነሻ ከነበሩት ምክንያቶች መካከል «በልማት ስም አርሶአደሮችን ማፈናቀል ያብቃ፣ ለተፈናቀሉትም በቂ ካሳ ይሰጥ» የሚል ሲሆን፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር የተፈናቀሉትን አርሶአደሮች በ5 አመታት ውስጥ ድጎማዎችን በማድረግ ችግራቸውን እፈታለሁ በማለት አዲስ እንቅስቃሴ ቢጀመርም፣ ከእንግዲህ የአርሶ አደሮችን መፈናቀል ለማስቀም ያዘጋጀው እቅድ የለም።

“በርካታ አርሶአደሮች ያለምንም ካሳ በግፍ ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎችም ተሰደዋል። በስራቸው አንቱ የተባሉ አርሶአደሮች ከይዞታቸው በድንገት መፈናቀላቸውን ተከትሎ ከእነቤተሰባቸው ለልመና ጭምር ተዳርገዋል የተዳረጉ ሲሆን፣ ይሰጣል የተባለው የካሳ ክፍያ ለሞቱት ቤተሰቦች እና ለተሰደዱት ሁሉ ያካትት አያካትት ግልጽ የሆነ ነገር የለም። የመልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን ተቋቁሟል በተባለ ማግስት አሁንም በርካታ አርሶአደሮች የይዞታ መሬታቸውን በልማት ስም እንዲለቁ እየተገደዱ ነው።

ከተፈናቃይ አርሶአደሮች የተወሰዱትን አብዛኞቹን የእርሻ መሬቶች ከአገዛዙ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው ግለሰቦች በርካሽ ዋጋ ይዘው ግንባታዎችን አካሂደውባቸዋል።