በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ደንብ ማስከበር ስልጠና ተሰጥቷቸው በማህበር የተደራጁ ወጣቶች እንዲበተኑ ተደረገ

ኢሳት (ታህሳስ 6 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ልዩ የትራንስፖርት የደንብ ማስከበር ስልጠና ተሰጥቷቸው በ21 ማህበራት የተደራጁ ከ300 በላይ ወጣቶች ያለአግባብ እንዲበተኑ መደረጉን የማህበሩ አባላት ለኢሳት አስታወቁ።

ከተደራጁና በተለያዩ የመዲናይቱ የትራስፖርት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከተሰማሩ ስድስት አመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አባላቱ ከታህሳስ 1, 2009 ዓም ጀምሮ ማህበራቸው እንዲበተን ውሳኔ እንደደረሰባቸው ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የደንብ ማስከበር ስራውን በዘመናዊ መልክ ያስተዳድራል የተባለ አዲስ ድርጅት 21 የሚሆኑትን ማህበራት ማፍረሱንና፣ ዘመናዊ ለተባለው አሰራርም የማህበሩ አባላት እንዳይታቀፉ መደረጉ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተበዳዮቹ ለኢሳት አስታውቀዋል። taxi

የማህበሩ አባላት አዲስ ተቋቁሟል ለተባለው ተቋም ጥያቄን ማቅረብ በጀመሩ ጌዜ 27 የማህበሩ አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ አባላት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከስድስት አመት በፊት የ2005 ምርጫ ሲቃረብ ወጣቶቹን በማህበር አደረጅቶ በመዲናይቱ በደንብ ማስከበር ስራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረጉ ይታወሳል።

የቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪዎች እንደሆኑ የሚናገሩት የደንብ ማስከበር ሰራተኞችቹ፣ በመንግስት ከተደራጁ በኋላ በማህበሩ በኩል ደሞዝ እየተከፈላቸው ግብር ሲከፍሉ መቆይታቸውን አክለው አስረድተዋል። ይሁንና ከታህሳስ 1, 2009 አም ጀሞሮ “ሁሉ” የተሰኘ እና የመብራትና የውሃ አገልግሎት ክፍያን የሚያስተዳድር ድርጅት ማህበራቱን እንደተረከበ ታውቋል።

ይኸው ተቋም ለምን እኛን ማቀፍ እንዳልፈልገ ግልፅ አልሆነልንም ሲሉ የገለጹት የማህበር አባላቱ ጥያቄያቸውን ባቀረቡ ጊዜ ለእስር እንዲዳረጉ መደረጉ ቅሬታን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ለእስር የተዳረጉ 27 የማህበር አባላት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ወረዳ 25 ፖሊስት ጣቢያ እንደሚገኙ ከአባላቱ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከፖሊስም ሆነ ከ “ሁሉ” ድርጅት ምላሽን ለማግኘት አልተቻለም።