በአወዳይ አምስት ሰዎችን የገደለው ግለሰብ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገደለ

ግንቦት ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በአወዳይ ከተማ 5 ሰዎችን በሽጉጥ ተኮሱ የገደለው አቶ አብዲ እድሪስ የተባለው የቀበሌ አስተዳዳሪ ማታ ከምሽቱ 3 ሰአት ላይ ከመስጊድ ሲወጣ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሏል። ወኪላችን እንደገለጸው በርካታ ጥይቶ ያረፉበት ግለሰቡ፣ ሰውነቱ በጥይት ተበሳስቷል ብሎአል።
ባለስልጣኑ ድርጊቱን ከፈጸመ በሁዋላ ለጥቂት ጊዜ ታስሮ የተፈታ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት እርምጃዎችን የወሰደው ራሱን ለመካለከል ባደረገው ሙከራ ነው በማለት ውሳኔ አሳልፎለት ነበር። ይህንኑ ተከትሎም የራስ መካለከያ የጦር መሳሪያ ተሰጥቶት ነበር።
ወኪላችን እንደሚለው ባለስልጣኑ ጥቃቱን የፈጸመው አምና የረመዳን ጾም በገባ በመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ሲሆን፣ የበቀል እርምጃውም በተመሳሳይ ሳምንት መወሰዱ ድርጊቱን አስገራሚ አድርጎታል።
ጥቃቱ በኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ላይ ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሯል። ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
ኢሳት በወቅቱ ግልሰቡ ስለፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ዘገባ አቅርቦ ነበር። የኢሳት ዘገባ በምስራቅ ሃረርጌ በአወዳይ ከተማ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የወረዳው አስተዳዳሪበከፈተው ተኩስ ሁለት ህጻናት እና አንድ ጎልማሳ ተገድለዋል። ነዋሪዎች ማምሻውን ለኢሳት እንደገለጹት ከሆነ የሟቾች ቁጥር 7 ድርሷል ብሎ ነበር።
የአወዳይ 01 ቀበሌ ሊቀመንበር የሆነው አቶ አብዲ እድሪስ በከፈተው ተኩስ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 3 ሰዎች መግደሉንና በድርጊቱ የተበሳጨው የከተማው ህዝብ ወደሊቀመንበሩ ቤት በማምራት ሁለቱንም መኖሪያ ቤቶቹን ማቃጠሉን፣ ሊቀመንበሩ ወደ ሃረር ሸሽቶ ሲያመልጥ ፌደራል ፖሊሶች ደግሞ ባለቤቱንና ልጆቹን ይዘው ከከተማማስወጣታቸውን ኢሳት በጁላይ 2 ፣ 2016 ዘገባው መግለጹ ይታወሳል።