በአርባምንጭ መምህራን የተቃውሞ አድማ አድርገዋል፣ 5 መምህራን የደረሱበት አልታወቀም

መጋቢት 17 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የኢሳት የአርባምንጭ ዘጋቢ እንደገለጠው ሀይሌ ደጋጋ እየተባለ በሚጠራው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ ተማሪዎች የመምህራን ድምጽ ይሰማ የሚል ተቃውሞ በማሰማታቸው የፌደራል ፖሊስ በሰፍራው ደርሶ በርካታ ተማሪዎችን ደብድቧል።

የፌደራል ፖሊስ እርምጃውን የወሰደው ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ከግቢ ለመውጣት ሲዘጋጁ በነበረበት ወቅት ሲሆን፣ ተማሪዎች በፌደራል እርምጃ በመበሳጨት በድንጋይ ለመከላከል ሞክረዋል። ከዚሁ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ አምስት መምህራን ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ መሰወራቸው ታወቓል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ መምህራን ባለፈው ሀሙስ  የደሞዝ ጭማሪውን በመቃወም አድማ መምታታቸው ይታወቃል። ከፍተኛ የሆነ ማስጠንቀቂያ  ቢደርሳቸውም በኮከበ ወ አጽብሀ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን አሁንም ስራ አልጀመሩም። በትናንትናው እለት ደግሞ ቦሌ ዶ/ር ሀዲስ አለማየሑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የካ ካራ አሎ አንደኛና ሁለተኛ ትምህርት ቤቶች የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

የመምህራን ማህበር ለገዢው ፓርቲ የወገነ በመሆኑ አድማውን በተቀናጀመ መንገድ ለማስቀጠል አለመቻሉን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ መምህር ለኢሳት ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተለያየ ጊዜ አድማውን እያደረጉ ናቸው። ምናልባት ሁሉም ትምህርት ቤቶች በአንድ ጊዜ አድማውን ቢያደርጉ የተሻለ ተጽእኖ ምፍጠር ይቻል ነበር ሲሉ መምህሩ አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ  የአማራ ክልል የሚገኙ  መምህራን የአዲስ አበባ መምህራን ተለይተው ተጠቂ እንዳይሆኑ ለመከላከል በማሰብ ተመሳሳይ እድማ ለመጀመር ውስጥ ለውስጥ ምክክር ጀምረዋል። እንቅስቃሴ የተጀመረባቸውን ትምህርት ቤቶች ለደህንነት ሲባል እንዲገለጥ ያልፈለጉት መምህራን ምናልባትም ከሁለት ቀናት በሁዋላ በአማራ ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ተመሳሳይ ተቃውሞች ሊጀመሩ ይችላሉ ብለዋል።

መምህራን እንደሚሉት የመገናኛ ብዙሀን የመምህራኑን የስራ ማቆም አድማ  ከደሞዝ ጥያቄ ጋር ብቻ እያያዙ የሚያቀርቡት ዘገባ ትክክል አይደለም። መምህራን እንደሚሉት የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ፣ የትምህርት ጥራት ፣ የትምህርት ነጻነት እና የመምህራንን የዜግነት መብት ጥያቄዎች በውስጡ አካቶ የያዘ በመሆኑ፣  ጥያቄዎች በተናጠል ሳይሆን በአጠቃላይ መልስ ማግኘት አለባቸው።

ባለፈው ሀሙስ በተጀመረው የመምህራን የስራ ማቆም አድማ የደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ 2ኛ ደረጃ፣ የጥቁር አንበሳ 2ኛ ደረጃ ፣ የኮልፌ 2ኛ ደረጃ፣ የደራርቱ ቱሉ መሰናዶ፣ የኮከበ ጽበህ 2ኛ ደረጃ፣ እና የአጋዚያን ቁጥር 3 ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ተሳትፈዋል።