በአሜሪካ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምርመራ የሚደረግባቸው የቻይና የቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛውን ድራሻ ይዘው በመስራት ላይ ናቸው ነው ተባለ

ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአሜሪካ  ኮንግረስ ፓናል ሁአዌይ እና ዜድ ቲኢ የተባሉት የቻይና የቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያዎች የሚጠቀሙባቸው የስለላ መሳሪያዎች ለአሜሪካ ደህንነት አስጊ በመሆናቸው መንግስት ልዩ ክትትል እንዲያደርግባቸው መጠየቁ፣ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት ከሳበ በሁዋላ እነዚህ ሁለት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ውስጥ ታላቅ ድርሻ እንዳላቸውና በሚቀጥሉት 2 አመታትም ከፍተኛ ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸው ታውቋል።

ዜቲኢ ኩባንያ ለኢትዮጵያ መንግስት የሞባይል ቴክኖሎጂን በማስፋፋት እና ለስለላ ስራ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመለገስ እንዲሁም ሳተላይት ሬዲዮኖችንና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለማፈን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን በመስጠት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ የሞባይል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት በሚል የ1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር ጫረታ ለዜት ቲኢና ለሀዋይ ኩባንያዎች መክፈቱን ብሉምበርግ ዘግቧል።

የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጺዮን ለብሉምበርግ እንደተናገሩት፣ መንግስት በእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ኢንቨስት የሚያድርግ ባለመሆኑ ና ኩባንያዎች የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው ምንም ችግር አይፈጠርም በማለት ሁለቱ ድርጅቶች በቅርቡ ታላቅ የሚባለውን የቴሌን ኮንትራት ሊጫረቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።