በአማራ እና በሃረሪ ክልሎች የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ድርቅ እንደመታው ተገለጸ

ግንቦት ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከግንቦት አራት ቀን ጀምሮ ልዩ ልዩ ጥቅማጥቆሞችን እንደሚሰጥ በመግለጽ፣ እየጠፉ በሚገኙ ወታደሮች ቦታ አዳዲስ ወታደሮችን ለመቅጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ያለው የህውሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ በተለይ በአማራ ክልል በሁሉም ከተሞች አንድም ተመዝጋቢ በመጥፋቱ ምዝገባውን ለማካሄድ የተመደቡ ሰራተኞች ግራ መጋባታቸውን ጥያቄ ያቀረበችላቸው የክልሉ ወኪላችን ገልጻለች።
ከወራት በፊት በየትምህርት ቤቱ በራፍ ላይ ማስታወቂያ በማውጣትና በብአዴን አባላት ቅስቀሳ በማድረግ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ በማሰናከል ለመመልመል የተደረገው ሙከራ በመምህራንና ትምህርት ባለሙያዎች ጥረት ከከሸፈ በሁዋላ፣ ገዢው ፓርቲ በአዲስ መልክ በየክፍለ ከተማው ወጣቶችን ለመመዝገብ ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ነው።
በመመልመያ መስፈርቱ ነጻ የትምህርት ዕድልና ተጨማሪ ጥቅማጥቅም እንደሚሰጥ ቢያውጅም፣ ወጣቱ ግን በእንቢተኝነቱ በመጽናት አንድም ሰው ለምዝገባ አለመምጣቱ እንዳስደነቃቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በምዝገባ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
በሃረሪም እንዲሁ ተመሳሳይ ሁኔታ መፈጠሩን ወኪላችን ተዘዋውሮ በመመልከት ለማረጋገጥ ችሎአል። ወጣቱ ከዚህ አገዛዝ ጋር አብሮ መቀጠል ፍላጎት የለውም የሚለው ዘጋቢያችን፣ በሁሉም የምዝገባ ጣቢያዎች የሚመዘጋቡ ወጣቶች በመጥፋታቸው መዝጋቢዎች ኮታውን ለመሙላት ተጨንቀዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰራዊቱን እየጣሉ የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፣ ከሚጠፉት መካከል ወታደራዊ አዛዦችም ይገኙበታል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከሰራዊቱ የተቀነሱ የቀድሞ ጦር አባላትም እንዲሁ ወደ ሰራዊቱ ተመልሰው እንዲቀላቀሉ ጥሪ የቀረበላቸው ቢሆንም፣ በእነሱ በኩል የሚሰጠው ምላሽም እጅግ ቀዝቃዛ ነው።
በተመሳሳይ ዜና አገዛዙ ለተቀናሽ ሰራዊት አባላት የመኖሪያ ቦታ እሰጣለሁ በማለት በየክፍለ ከተማውና ቀበሌ ጽህፈት ቤቶች ምዝገባ ቢጀምርም፣ በየወረዳው ያሉ አመራሮች ክብር የሚነካ ስድብ እየሰደቡን አላስተናገዱንም ብለዋል።
መመሪያው በሚያዘው መሠረት ገንዘብ ከመቆጠብ አልፈው ለሚነሱ አርሶአደሮች የሚከፈለውን የመሬት ካሳ ክፍያ ለመሸፈን ዝግጅት እንዳደረጉ የሚናገሩት በማህበር የተደራጁት ተቀናሽ ሰራዊት አባላት የመከለከያ ሰራዊቱ አመራሮች በማህበራት ስብሰባ እንዳይገኙ መከልከላቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
“እናንተ አትፈለጉም” በሚል በስብሰባ እንዳይካፈሉ ክብርን በሚነካ ሁኔታ በዕለቱ ስብሰባውን በሚመሩ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች መገለላቸው እንዳሳዘናቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡
የገዥው መንግስት በሚፈጠሩበት ህዝባዊ አመጾችና ግጭቶች ጊዜ ድረሱልን በሚል ጊዜ ፈጥነው በመገኘት እገዛ ሲያደርጉ እንደነበሩ የሚናገሩት ተመላሽ የሰራዊት አባላት፣ አመራሮች ከተጠቀሙባቸው በኋላ ክብራቸውን መንካታቸው ዳግም ወደ ውትድርናው ዓለም በመቀላቀል ዕርዳታ የማድረግ ፍላጎታቸውን እንዳጠፋው ተናግረዋል፡፡