በአማራና በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተበጀተው የወጣቶች በጀት ለባለስልጣናት መበልጸጊያ እየዋለ ነው ተባለ

ሰኔ ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በአማራና በኦሮምያ የነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት 11 ቢሊዮን ብር ለወጣቶች እንዲከፋፈል መመደቡን ቢያስታውቅም ወጣቶች ግን ያየነው ገንዘብ የለም፣ ገንዘቡን የሚጠቀሙበት ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
“ ሀገሪቱ በወጣት ጡረተኛ ተሞልታለች” ያሉት የደብረማርቆስ ወጣቶች፣ “ አረጋውያን እናት አባት መጦር እየተገባን እኛ ራሳችን የወጣት ተጠሪዎች ሆነናል” ይላሉ።
“የአመራሩ ወገን ብቻ የሚደራጅበት አሰራር ነው ፤ በአድሎ እና በማገለል ላይ የተመሰረተው አሰራር ድሃውን ወጣት አማሮታል “ የሚሉት ወጣቶች፣ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ጉዳዩ ወደ ፖለቲካ እየዞረ እየታሰሩ መሆኑን ገልጸዋል
“በጀቱ የተበጀተው ለሃብታሞች እንጅ ለድሆች አይደለም” የሚለው ሌላው ወጣት፣ በጣም የሚገርመው፣ ገንዘብ ለመቀበል 6 ሺ ብር እና የቦታና የቤት ካርታ እንዲያስይዙም እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።ከሁሉም በላይ በህብረተሰቡ ውስጥ የደሃ ደሃ የሚል ስያሜ ተፈጥሮ፣ የደሃ ልጆች የስነ ልቦና ችግር እንዲደርስባቸው እየተደረገ መሆኑን ወጣቶች ተናግረዋል።
የከተማው ህዝብ ውሃ የሚያገኘው በሁለት ሳምንት መሆኑን፣ መብራትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሉ ማለት እንደማይቻል ነዋሪዎች ተናግረዋል።