በባለስልጣናትና በህዝቡ አለመግባባት ሳቢያ፤ በሀዲያ የተጀመረው ስብሰባ ተቋረጠ

ጥር 30 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ፍኖት ዘገባ፤በመልካም አስተዳደር እጦትና በመሬት ወረራ ዙሪያ በሀዲያ ዞን የተጀመረው ስብሰባ የተቋረጠው፤ መድረክ ሲመሩ በነበሩት ባለስልጣናትና በተሰብሳቢው ህዝብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት፤ ህዝቡ ስብሰባውን ረግጦ በመውጣቱ ነው።

የክልሉ እና የዞኑ አመራሮች በተገኙበት በሆሣዕና ከተማ ባለፈው እሁድ ጥር 14 ቀን 2004 ዓ.ም በሀዲያ የባህል አዳራሽ የተጠራው ይህ ስብሰባ፤ በዞኑ ስላለው የመልካም አስተዳደር እጦትና የመሬት ወረራ ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያዬት የታሰበ ነበር።

ይሁንና፤ በስብሰባው ለመሳተፍ የሄዱት ነዋሪዎች በዞኑ ከፍተኛ አመራርነችና በከተማው አስተዳደር ቦታ ተቀምጠው ከፍተኛ የሙስና ተግባር እና ብልሹ አሰራር የፈፀሙ አካላትን ስም ከነድርጊታቸው ሲገልፁ አወያዮቹ፦ “የሰው ስም አትጥቀሱ፤ ስማቸውን ስትጠቅሱ ስብዕናቸውን እየነካችሁ ነው፣ችግሮቻችሁን ብቻ ጥቀሱ”ማለታቸው ተሰብሳቢውን ቅር ማሰኘትና ማስቆጣት እንደጀመረ በስፍራው የነበሩ ታዳሚዎች ተናግረዋል።

የአወያዮቹ ምላሽ ያስቆጣው ሕዝብም ፦“ታዲያ ለምን ጠራችሁን? በአንድ ቦታ ሙስና የፈፀሙትን የቦታ ለውጥ በማድረግ በክልል ደረጃ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እያደረጋችሁ እየሾማችሁና እያበረታታችሁ ሳለ፤ እናንተ ያልታረማችሁትንና ያላረማችሁትን እኛ ምን እንድናደርግ ነው የምትፈልጉት?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።

የስብሰባው አንድ አጀንዳ ስለመልካም አስተዳደር እስከሆነ ድረስ፤የመልካም አስተዳደር ፀር የሆነውና በክልሉ በስፋት እየታዬ ያለው ሙስና በስብሰባው በጥልቀት ሊፈተሽ ሲገባው በአወያዮቹ በኩል የታየው የማድበስበስ ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነበር ይላሉ አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ለኢሳት ስለጉዳዩ ሲናገሩ።
ይህ የሆነውም በዞኑ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና እንደፈፀሙ የሚወራባቸው የደቡብ ክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ መለስ ዓለሙ በስብሰባው በመገኘታቸው እርሳቸውን ለመከላከል ነው-የስብሰባው ተሳታፊዎች እንዳሉት።

ተሰብሳቢው ህዝብ ግን እንዳጀማመሩ ሙስናንና ሙሰኞችን መኮነኑን ቀጠለ ያሉት የስብሰባው ተሳታፊዎች፤ በሁኔታው ቅር የተሰኙት የክልሉና የዞኑ በድጋሚ ሀሳብ የሚሰጡ ሰዎች የሰው ስም እንዳይጠቅሱ ሲያስጠነቅቁ፤ተሳታፊው ሕዝብ በንዴት ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን ገልጸዋል።