በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የወጣባቸውና 25ሺ ያህል እስረኞችን የሚይዙ አዳዲስ ወህኒ ቤቶች በአራት ክልሎች ተገነቡ

ኢሳት (ሰኔ 20 ፥2009)

በቢሊዮን ብሮች ወጪ 25 ሺህ ያህል እስረኞችን የሚይዙ ወህኒ ቤቶች በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በዝዋይና በሸዋሮቢት መገንባታቸው ታወቀ። አዲስ ፎርቹን የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው የአዲስ አበባ እስር ቤት 900 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን በአንድ ጊዜ 6 ሺህ እስረኞችን የመያዝ አቅም አለው።

በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አባሳሙኤል ወንዝ አቅራቢያ በ5ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር ላይ የተዘረጋው ይህ ወህኒ ቤት ስራው የተጀመረው በሰኔ ወር 2006 መሆኑም ተመልክቷል።

የእስረኞቹ ማቆያ እያንዳንዳቸው ሁለት ፎቅ ያላቸው 5 ብሎኮች ሲሆኑ እያንዳንዱ ብሎክ 1ሺህ 200 እስረኛ እንደሚይዝም ተመልክቷል።

ግንባታው 95 በመቶ ተጠናቋል የተባለውና 6ሺህ እስረኞችን የመያዝ አቅም ያለው ወህኒ ቤት CCTV  ካሜራዎችን ጨምሮ የምስጢር የድምጽና የምስል መቅረጫዎች የተገጠሙበት እንደሆነም ተገልጿል። በሕወሃቱ የጦር ጀኔራል ሜ/ጀኔራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ የሚመራው ኢንሳ ወይንም የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የስራው መሳሪያዎቹን የመትከሉን ሃላፊነት እንደወሰደም መረዳት ተችሏል።

የፌደራሉን መንግስት እስር ቤቶች የመገንባቱ ስራ ከአዲስ አበባ ባሻገር በድሬዳዋ፣ በሸዋሮቢትና በዝዋይ መቀጠሉና መጠናቀቁም ታውቋል።

በሸዋሮቢት 4ሺህ 800 እስረኞችን የሚይዝ ወህኒ ቤት የተገነባ ሲሆን በድሬዳዋም በተመሳሳይም 5ሺህ ያህል እስረኞችን የሚይዝ ወህኒ ቤት መሰራቱም ተመልክቷል።

በዝዋይ የተገነባው ወህኒ ቤት ከአዲስ አበባው ጋር በተመሳሳይ መጠን 6ሺህ ያህል እስረኞችን የሚይዝ መሆኑን ከአዲስ ፎርቹን ዝርዝር ዘገባ መረዳት ተችሏል።