በቅርቡ በሚከበረው የእሬቻ በአል አንድም የታጠቀ ፖሊስ ወይም ወታደር እንደማይሰማራ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 14/2010)በኦሮሚያ ቢሾፍቱ ከተማ በቅርቡ በሚከበረው የእሬቻ በአል አንድም የታጠቀ ፖሊስ ወይም ወታደር እንደማይሰማራ የክልሉ መንግስት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሳተፉበታል በተባለው የእሬቻ በአልን ለመቆጣጠር ያልታጠቁ 3 መቶ ወጣቶች ብቻ እንደሚሰማሩ ገልጿል።

ባለፈው አመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ መተፋፈግ መገደላቸው ይታወሳል።

ዘንድሮ ምንም አይነት ፖሊስ በአካባቢው አይደርስም መባሉ ላለፈው እልቂት ተጠያቂው እራሱ መሆኑን አገዛዙ ማመኑን ያሳያል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል የእሬቻ በአልን ለማክበር ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ ቢሾፍቱ ከተማ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ይተማሉ።

በአሉ የዝናብ ወቅት አብቅቶ የሰብል መሰብሰቢያ ጊዜ በመሆኑ ምስጋና ለማቅረብ የሚደረግ የኦሮሞ ባህላዊ በአል ነው።

ባለፈው አመት መስከረም 22/2009 የአገዛዙ ወታደሮችና ታጣቂዎች ጸጥታ ለማስጠበቅ በሚል ሰበብ በሔሊኮፕተር የታገዘ ጋጋታና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በመኖሩ በአሉ ወዲያውኑ ነበር የደፈረሰው።

በወቅቱ የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞና ቁጣ አገዛዙን ማስፈራቱ በበአሉ ተሳታፊዎች ላይ ጥይት ለመተኮስ ምክንያት ሆኗል።

እናም በተኩሱ ሰዎች በመገደላቸውና ይህንኑ ተከትሎ በነበረው መተፋፈግ ገደል ገብተው የሞቱ በርካታ ሰዎች ነበሩ።

በበአሉ ላይ በጥይት የተገደሉትን ጨምሮ 8 መቶ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።አገዛዙ ግን የሟቾጭ ቁጥር 52 ብቻ ነው ይላል።

ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ አለም አቀፍ ግፊት ቢደረግም የአገዛዙ ባለስልጣናት እስካሁን ፈቃደኛ አልሆኑም።

ዘንድሮ ማለትም በመጭው መስከረም 21/2010 የሚከበረው ይህው የእሬቻ በአል ያለፈው ስህተት እንዳይደገም የአገዛዙ ባለስልጣናት ጥንቃቄ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

ለዚህ ደግሞ ላለፈው ስህተት ዋነኛ ምክንያት የሆኑት የአገዛዙ ወታደሮች ወደ በአሉ ድርሽ እንደማይሉ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ባለፈው ለተገደሉት እስካሁን ተጠያቂ የሆነ አካል ባይኖርም ዘንድሮ ስህተቱ እንዳይደገም ከጸጥታ ሃይሎች ይልቅ 3 መቶ ወጣቶች በስነ ስርአት አስከባሪነት እንደሚመደቡ ተገልጿል።

ወጣቶቹን ማን እንዳዘጋጃቸውን ግን የታወቀ ነገር የለም።በአገዛዙ ዘንድ ትልቅ ስጋት የደቀነው ባለፈው የሞቱትን ሰዎች ለማስታወስ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ይጠራል መባሉ ነው።

8 መቶ ሰዎች የሞቱበት የእሬቻ በአልን ትልቅ የሰማእታት ቀን መታሰቢያ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።