በሶሪያ የተፈጸመውን የኬሚካል ጦር መሳርያ ጥቃት ተከትሎ የተመድ ጸጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በሶሪያ መንግስት ተፈጽሟል የተባለን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃትን ተከትሎ ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።

አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራባውያን ሃገራት 20 ህጻናትን ጨምሮ ለ72 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት የባሽር አልአሳድ መንግስት ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል።

የሶሪያ የጦር አውሮፕላኖች ማክሰኞ በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ፈጽመውታል የተባለው ጥቃት በተጎጂዎች ላይ ከፍተኛ ስቃይ ማድረሱን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአለም ሃገራት ማክሰኞ ለተፈጸመው ጥቃት ሶሪያን ተጠያቂ ቢያደርጉም የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ባሽር አልአሳድ የኬሚካል ጥቃቱ በአማጺያን የተፈጸመ ነው ሲሉ ድርጊቱን አስተባብለዋል።

የሶሪያ አጋር የሆነችውና በሃገሪቱ በአማጺያን ላይ የሚካሄድ ወታደራዊ ዘመቻ እንደደገፈች የምትገኘው ሩሲያ በበኩላ የሶሪያ መንግስት በአማጺያን ይዞታ ስር ያለን መሳሪያ ማምረቻ ተቋም ባጠቃ ጊዜ የኬሚካል መሳሪያን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጻለች።

ይሁንና ጥቃቱ በተፈጸመት ግዛት የሚኖሩ ነዋሪዎች እና ምዕራባዊያን ሩሲያ ያቀረበችውን ማብራሪያ ውድቅ አድርገውታል።

በዚሁ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ለህመም ተዳርገው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል።

ከተጎጂዎቹ መካከል አብዛኞቹ መተንፈስ አቅቷቸው አፋቸው በአረፋ መሞላቱን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

የመጀመሪያው የአየር ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ርብርብ በመደረግ ላይ እንዳለ ተጨማሪ ጥቃት መፋጸሙን ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አስታውቀዋል።

በዚሁ የኬሚካል ጥቃት ከአለም አቀፉ ዙሪያ መስተጋባት የጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ረቡዕ እንዲካሄድ ወስኗል።

የምክር ቤቱ አባላት ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በሚያካሄዱት በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ በኬሚካል ጥቃቱ ዙሪያ ሪፖርቱን በማድመጥ በቀጣይ መወሰድ በሚኖርበት እርምጃ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የብሪታኒያና የጀርመን መሪዎች ሩሲያ ጥቃቱን አስመልክቶ የሰጠችው ማብራሪያ በተጨባጭ እንድታስረዳ አሳስበዋል። በግዛቱ ያሉ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች በበኩላቸው ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ምንም አይነት ወታደራዊ ጣቢያና የመሳሪያ ማምረቻ አለመኖሩን እንደገለጸ ቢቢሲ ዘግቧል።

የኬሚካል ጦር መሳሪያ ባለሙያ የሆኑት ኮሎኔል ሃሚሽ ዴ-ብሬተን ጎርዳን ሩሲያ ያቀረበችው መረጃ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።

ስድስተኛ አመቱን ባስቆጠረው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን ድረስ ወደ 300 ሺ አካባቢ ሰዎች መሞታቸውን አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሶሪያውያን ደግሞ ሃገራቸው ለቀው እንደወጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።