በሶማሌ ክልል በዶሎ ዞን ባለፈው ወር ብቻ በርሃብ ምክንያት 68 ሕጻናት መሞታቸውን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታወቀ

ሐምሌ ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የተከሰተው የርሃብ አደጋ ወደ አስጊ ደረጃ መሸጋገሩን እና በርሃብ ምክንያት ባለፈው ወር በሶማሌ ክልል በዶሎ ዞን 68 ታዳጊ ሕጻናት መሞታቸውን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታወቀ። በክልሉ ከድርቁ በተጨማሪ ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋዎች በመከሰታቸው የረድኤት ሥራውን ይበልጥ ውስብስብ አድርጎታል።
በድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በቀጠናው ላለፉት 12 ዓመታት በረድኤት አገልግሎት ሥራ ላይ የተሰማሩ ቢሆንም እንደ ዘንድሮው ዓይነት አደገኛ የርሃብ አደጋ ተከስቶ እንደማያውቅ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።
”በመላው ዓለም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የርሃብ ተጋላጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የበሽታ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል።” ሲሉ በድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን የቀጠናው አስተባባሪ ታራ ኔዌል አስታወቀዋል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሶማሌ ክልል የተከሰተው የድርቅ አደጋ በመጪዎቹ ወራት ውስጥ ይበልጥ እየከፋ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ ርሃቡ አድማሱን እያሰፋ የመጣ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ እና በኬንያ የዝናቡ መጠን ከ70 ከመቶ በታች እንደሚቀንስ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስታውቀዋል። በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ ባለፉት 36 ዓመታት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አናሳ የዝናብ መጠን ተከስቶ አያውቅም።
አርብቶ አደሮች በድርቁ ምክንያት ዝናብ ባለመኖሩ የቤት እንስሳቶችች ሞተዋል። ሰብሎቻቸው ደርቀዋል፣ የመጠጥ ውሃ ማግኘትም ተስኗቸዋል። ንጹህ የመጠጥ ውሃ አለመኖሩን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ለውሃ ወለድ በሽታዋች ተጋላጭ ሆነዋል። በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ውሃ የቀላቀለ ተቅማጥ፣ የኮሌራ ወረሽኝ ታማሚ ሆነዋል። ይህም የአርብቶ አደሮችን ሕይወት ከፍተኛ ተግዳሮት ላይ እንደሆኑ ያሳያል ሲል የህክምና ቡድኑ በሪፖርቱ አመላክቷል።
”አብዛሃኛው የቤት እንስሳቶቻቸው ሞተውባቸዋል። ሁኔታዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት መስጠት አይቻልም። በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ ይጥላል። ይህም በመሆኑ የነዋሪዎቹ ሕይወት ለማትረፍ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል።” ሲሉ ታራ ኔዌል አክለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 7.8 ሚሊዮን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያሉ ሲሆን ቁጥሩ በሁለት ሚሊዮን ሊያሻቅብ ይችላል ተብሎ ይገመታል። የረድኤት ድርጅቶች ያላቸው የምግብ ክምችት እየየተሟጠጠ በመሆኑ በኢትዮጵያዊያን የርሃብ ተጠቂዎች ካሁኑ በከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ሳይገቡ እገዛ ሊደረግላቸው ይገባቸዋል ሲል ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድንን በመጥቀስ ቪኦኤ ዘግቧል።