በስልጣን ላይ ያሉ ተሿሚ አመራሮች ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዕውቀት የሌላቸው ናቸው ሲሉ አሰልጣኞች ተናገሩ፡፡

የካቲት ፮ ( ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በጥልቅ ተሃድሶ በመሰልጠን ሀገሪቱ ከወደቀችበት አዘቅት ነጻ ያወጣሉ ተብሎ የታመነባቸው አመራሮች ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዕውቀት የሌላቸው መሆኑን አንድ አሰልጣኝ በተለይ ለኢሳት ተናገሩ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አመራሮችን በማሰልጠን የተሳተፉት ግለሰብ እንደተናገሩት አመራሮች ለስልጠና ከመግባታቸው በፊት በተሰጣቸው የሀገሪቱን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሚዳስሰው የመግቢያ ፈተና አብዛኛው ሰልጣኝ የግንዛቤ ችግር አለበት።
በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት አመራሮች ብዙም የአመራር እውቀት እንደሌላቸው የሚናገሩት አሰልጣኝ፣ ወደ ሹመት እየመጡ ያሉት ግለሰቦች በበቂ ሁኔታ ህዝብን የመምራት አቅም ያላካበቱ ናቸው ይላሉ። በአሁኑ ለጥልቅ ተሃድሶ በመሰልጠን ላይ ያሉ አዳዲስ አመራሮችም፣ የእውቀት ችግር እንዳለባቸው የሚያምኑት አሰልጣኙ፣ እንኳን አዳዲስ አመራሮች ይቅርና፣ በአሰልጣኝነት የተመረጡት ሳይቀር በቂ እውቀት የሌላቸው ናቸው ይላሉ።
የሃገሪቱ ዋና ችግር የሆነው ሙስና በአዲሱ አመራር ላይም ይታያል ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል