በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ኤንባሲ ውስጥ በመግባት ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

የካቲት ፫ ( ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሱዳን ውስጥ ለሚፈጸምባቸው ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ኤንባሲው ለስደተኞች ምንም ዓይነት እገዛ አለማድረጉን በመቃወም ኤንባሲው ግቢ ውስጥ በመግባት በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ኢትዮጵያውያኑ ኤንባሲው አካባቢ ያሉ የደህንነት አባላት በቪዲዮ ምስል እንዳይቀርጹ ካሜራዎችን በመቀማት ለመከልከል ሙከራ አድርገዋል። ኢትዮጵያን ስደተኞች በሱዳን በኡንዱርማን እና በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ አስታዋሽ አጥተው የተጣሉ ሲሆን ኢትዮጵያን ዜጎች ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው እንደሌሎች አገራት ኤንባሲዎች ከለላ አያደርግልንም ብለዋል።
በሱዳን ፖሊሶች እና የፀጥታ ሃይሎች ሕጋዊ መኖሪያ መታወቂያቸውን ተነጥቀው ይታሰራሉ። በእስር ላይ ያሉ ስደተኞች ክፍያ ካልፈጸሙ ከእስር አይለቀቁም። በእስር ላይ ከሚገኙት እና የሚከፍሉት ገንዘብ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ወደ አገራቸው መመለስ አይችሉም። የኢትዮጵያ ኤንባሲም እስረኞቹን ስፍራው ድረስ በመሄድ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከጽሁፍ ውጪ የሰላማዊ ሰልፈኞችን ወኪሎች ለማነጋገር ፈቃደኝነታቸውን አላሳዩም በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።