በርካታ የዶርዜ ብሄረሰብ ተወላጆች በሽብርተኝነት ተከሰሱ

ጥር ፬ (አራት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የማንነት ጥያቄ አንስታችሁዋል በሚል ከ35 በላይ የዶርዜ ተወላጆች ላለፉት 2 ወራት በአርባምንጭ እና በጨንጫ  እስር ቤቶች ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

የዶርዜ ተወላጆች በአካባቢያችን ልማት የለም፣ መብታችንም አይከበርም በማለት ጥያቄያቸውን ከጠ/ሚኒስትሩ እስከ ፌደሬሼን ምክር ቤት አቅርበዋል። ዋና ዋና የሚባሉት የዶርዜ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች እየተፈለጉ በመታሰር ላይ መሆናቸውም ታውቋል። የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው እነዚህ ሰዎች፣ በባህላዊ ጭፈራቸው ላይ ጦር ይዘው መውጣታቸው ለሽብርተኝነት አንድ ማስረጃ ሆኖ ቀርቦባቸዋል። እስረኞች ከፍተኛ ለሆነ የምግብና የውሃ ስቃይ እየተደራጉ ነው።

የአካባቢው ካድሬዎች በጋሞና በዶርዜ መካከል ግጭት ለመፍጠር ለአመታት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ። ኮማንድ ፖስት እየተባለ የሚጠራው ወታደራዊ እዝ በአርባምንጭና አካባቢዋ 80 የሚሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን አስረው፣ የተወሰኑት ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስልጠና በሚል  ሲዳማ ዞን ወስጥ ወደ ሚገኘው ኦቦቶ ወደሚባል ቦታ  እስር ቤት ሲወሰዱ፣ 6 የሚሆኑት ደግሞ ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ለብቻ እንዲታሰሩ ተደርጓል።

በአርባምንጭና አካባቢው ካለው ከፍተኛ ሙቀት አንጻር በሽታ እየተስፋፋ መምጣቱ በእስረኞች ህይወት ላይ ችግር መፈጠሩን እንዲሁም  ቤተሰቦቻቸው እስረኞች ስላሉበት ሁኔታ ለመጠየቅ አለመቻላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመረጃ ስርቆት እንዲቆም እስረኞች ጠይቀዋል። በደቡብ ኦሞ ዞን በጅንካ ከተማ ታስረው የሚገኙ 10 የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ለደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት በጻፉት ደብዳቤ

በተያዙብን ላፕቶፖቻችን ውስጥ የሚገኙትን መረጃዎች፣ ፋይሎችና ፕሮግራሞችን እንፈትሻለን በሚል የመረጃ ስርቆት መፈጸሙን እንዲሁም የነበሩትን መረጃዎች በመቀየርና አዳዲስ መረጃዎችን ለመጫን ሙከራ መደረጉን በመጥቀስ ይህን ተግባር የፈጸሙት ሰዎች በህግ እንዲጠየቁላቸው ጠይቀዋል።

በህዝብ ደህንነቱ በአቶ አልአዛር ቶይሳና ከዞኑ ምክር ቤት የኮምፒዩተር ባለሙያ ነው ተብሎ የመጣው አቶ ክብሮም እቁባይ ዋና አቀናባሪነት ፣ የፌደራል ፖሊስ የጂንካ ሃይል አዛዥ ኮማንደር ጎሹ እና ምክትላቸው እንዲሁም፣ የዞኑ ኮማንድ ፖስት ወንጀል መርማሪ የተባሉት ኮንስታብል መልካም፣ ኢንስፔክተር ሃይሉና ኢንስፔክተር ትእዛዙ ምስክር ባሉበት የመረጃ ስርቆት መፈጸሙንና የሃሰት መረጃዎችን ለመጫን ሙከራ መደረጉን ዘርዝረዋል።

እስረኞቹ ፣ ከእኛ ተወስደው በፖሊስ እጅ ተይዘው በሚገኙት በማንኛቸውም የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ የሚደረጉ ቆርጦ ልጠፋዎች አማካኝነት ተጠያቂ እንደማይሆኑ አስታውቀዋል።

ደብዳቤውን ከጻፉት መካከል መ/ር አለማየሁ መኮንን፣ መ/ር እንድሪስ መናን፣ አቶ መሃመድ ጀማልና አቶ ስለሺ ጌታቸው ይገኙበታል።