በምስራቅ ኢትዮጵያ በምግብ እጥረት የተጠቁ ሕጻናት አስር እጥፍ መጨመሩን እና 67 ሕጻናት በርሃብ መሞታቸውን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታወቀ

ሰኔ ፲፱( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦጋዴን ዶሎ ዞን ያለው የርሃብና ያልተመጣጠነ ምግብ እጥረት አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን በአካባቢው የተሰማራ የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታወቀ።
”ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ በዶሎ ዞን ነዋሪ የሆኑ ታዳጊ ሕጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋላጭ ሆነዋል። የሕክምና ቡድናችን ባለፉት አስር ዓመታት በአካባቢው የሥራ ቆይታችን እንደዚህ ዓይነት ዘግናኝ ርሃብ አጋጥሞት አያውቅም።” ሲሉ የድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን የቀጣናው አማካሪ የሆኑት ሳሲካ ቫንደር ካም የችግሩን አሳሳቢነት አጽኖት በመስጠት ገልጸዋል።
የህክምና ቡድኑ ከኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር 27 ታክመው የሚወጡበት ማገገሚያ ጣቢያዎች እና አራት የመታከሚያ ማእከላት ተገንብተው ለርሃብ ተጠቂ ሕጻናት የምግብ መመገብ ሥራቸውን ጀምረዋል።
የድንበር የለሽ የሃኪሞች የሕክምና ቡድኑ በኦጋዴን በሚገኙ በዳኖድ፣ ሊህል ዩኩብ፤ ዋርዴር፣ ጋላዲ ዳራቶሌ በሚገኙ አካባቢዎች ነዋሪ ለሆኑ 6 ሽህ 136 ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ የምግብ እጥረት ተጠቂዎች ታዳጊ ሕጻናት ካለፈው ጃንዋሪ ወር ጀምሮ አገልግሎት ሰጥቷል። በተጨማሪም ለ491 ሕጻናት የህይወት ማዳን ሕክምና እንዲያገኙ የተደረጉ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አስር እጥፍ እንደጨመረ የህክምና ቡድኑ ጥናታዊ ሪፖርት አመላክቷል።
በያዝነው ሰኔ ወር ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በርሃብ ክፉኛ የተጎዱ 322 ሕጻናት የህክምና እና የምግብ አገልግሎት አግኝተዋል። ከእነዚህ ሕጻናት መካከል የሃምሳ አንዱን ሕይወት መታደግ አልተቻለም።በአጠቃላይ በሰኔ ወር ውስጥ ብቻ ጉዳተኛ ሆነው ተኝተው ሕክምናቸውን ከሚከታተሉ ታዳጊዎች ውስጥ በድምሩ 67 ሕይወታቸውን አጥተዋል።
”የ67 ታዳጊ ሕጻናት ሞት የሚያሳየው ነገር ቢኖር የችግሩን የከፋ ደረጃ መድረስ ነው። ለዛም ነው የሰብዓዊ አገልግሎት አቅርቦቱ በአፋጣኝ ተግባራዊ መሆን ያለበት።” በማለት ወ/ሮ ሳሲካ ቫንደር ካም የሰብዓዊ ቀውሱን አሳሳቢነት የሚያአስረዱት።
በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች በድርቁ ምክንያት መኖሪያ ቀያቸውን በመተው ወደ መጠለያ ጣቢያዎች በመግባት ላይ ናቸው። በርሃቡ ምክንያት ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና ምግብ ፍለጋ ከሦስት ዓመት ልጃቸው ጋር ወደ መጠለያ ጣቢያው የመጡት ወ/ሮ ፊርዶስ ስለሁኔታው አሳሳቢነት ሲናገሩ ”እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከዚህ በፊት አይቼ አላውቅም። ሁሉንም ነገር ይሰጡን የነበሩት የቤት እንሶቻችን አልቀውብናል። አሁን ምንም የለንም። ልጆቻችን በርሃብ ምክንያት ታመው እየሞቱብን ነው።” ብለዋል። በቀጠናው ድርቅ የተለመደ ክስተት ቢሆንም እንደዚህ በተከታታይ ሁለት የዝናብ ወቅቶች የተከሰተበት ወቅት አለመኖሩን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
የድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን የቀጣናው አማካሪ የሆኑት ሳሲካ ቫንደር ካም አክለውም ”የቤት እንስሳቶቻቸው በማለቃቸው ምክንያት ነዋሪዎቹ ልጆቻቸውን ወተት መመገብ አልቻሉም። ካለ ከብቶቻቸው ምንም ዓይነት የመኖር ዋስትና አማራጮች የላቸውም። ምግብና ውሃ ማጓጓዝም ተቸግረዋል። ነዋሪዎቹ በራችንን በማንኳኳት ምግብ ስጡን እያሉ ይለምኑናል።” በማለት የድርቁን አሳሳቢነት ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳደር በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተጎጂዎች የሚያቀርበው ምግብ በቂ አይደለም። ይህም በድርቁ ምክንያት ከፈለሰው ሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታውቋል። ባለፈው የዓለም የምግብ ድርጅት ፋኦ በበኩሉ በኦጋዴን ብቻ 1.7 ሚሊዮን በላይ አፋጣኝ እለታዊ የምግብ እርዳታ ጠባቂ የድርቅ ተጠቂዎች መኖራቸውን ሪፖርት አቅርቧል። አሁን ያለው የምግብ ክምችት ተሟጦ እያለቀ በመሆኑ ለጋሽ የረደኤት ድርጅቶች አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጡ በቀጠናው ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ሲል ማስጠቀቁ ይታወሳል።
የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን የእርዳታ ማእከላትን በጃራ እና ኒጎቦ ዞኖችንም እንደሚከፍት እና የአካባቢውን ሕጻናት ሕይወት ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ መደረግ ይገባዋል ሲል ድርጅቱ ሪፖርቱን አጠቃልዋል።