በሚኒሶታ ለኢሳት ቴሌቭዥን የተሳካ የገቢ ማሰባሰብ ተደረገ

መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የዘ ሀበሻው ሮቤል ሔኖክ እንደዘገበው  የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንን በገንዘብ ለማጠናከር በሚል ዋና ዓላማ በሚኒሶታ የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተካሄዷል።

አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነን፣ አባ ወልደተንሳኤን እና አባ ገብረማርያምን፣ እንደዚሁም ተወዳጁን ድምጻዊ ተሾመ አሰግድን የክብር እንግዶች በማድረግ የተዘጋጀው ይኸው የራት ምሽት ላይ መድረኩን በሚመራው በጋዜጠኛ ሔኖክ ዓለማየሁ ነበር የተከፈተው። በኢትዮጵያ ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን ራሱን አቃጥሎ ላጠፋው መምህር የኔሰው ገብሬ፣ በጋምቤላ ሰሞኑን ለተገደሉት ከ19 በላይ ነጹሐን ዜጎች፣ በቅርቡ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ደጃፍ ጸጉሯን እየተነጨች በአደባባይ የሚያድናት ወገን አጥታ ስትጎተት የነበረችውና ራሷን አጠፋች ተብሎ ዜናዋን ለሰማነው ለእህታችን ዓለም ደቻሳ፣ እንደዚሁም በቅርቡ በሚኒሶታ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ሁልጊዜም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ጋዜጠኞች እንዳይጎሳቆሉ፣ መልካም አስተዳደር በሃገራችን እንዲሰፍን ሲታገል ለነበረው ለአቶ ብርሃኔ ወርቁ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት እንዲደረግ በጠየቀው መሰረት ለነዚህ ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ የአንድ ደቂቃ ጸሎት ፕሮግራም ተደርጎ የገቢ ማሰባሰቡ ምሽት ተከፈቷል።

ከዚያም የቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ገብረሚካኤል ተሰማ ይህን ዝግጅት በጸሎትና በንግግር የከፈቱ ሲሆን እርሳቸውም  “የሃይማኖት መሪዎች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የለባቸውም” ተብሎ በአንዳንድ የእምነት ተከታዮች ለሚጠይቁ ጥያቄዎች የክርስትና እምነት የሃይማኖት መሪዎች ከተበደሉት እና ከተገፉት ሕዝብ ጋር ቁሙ እንደሚል አውስተው “ሕዝብ ከመሬቱ ሲፈናቀል፤ የዋልድባ ገዳም ሲታረስ፣  የሃይማኖት መሪዎች ዝም ብሎ ማየት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።  “ በዚህ ጭንቅ ሰዓት ከመሬቱ ከተባረረው፣ በሃገሩ ላይ ስደተኛ ለሆነው፣ ለተቸገረው፣ ስለሰው ልጅ መብት ጻፍክ ተብሎ ከታሰረው፣ ከታረዘው ጋር አብሮ መቆም ያስፈልጋል” በማለት ለሃይማኖት አባቶችም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከሳቸው በመቀጠል ታዋቂው የወንጌል ሰው አባ ወልደትንሣኤ ወደ መድረኩ ተጋብዘው “ኢሳት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልክ እንደ ሲኤን ኤን እና አልጀዚራ ተሰሚነት እንዲኖረው ቁልፉ ያለው በኛ በሕዝቡ እጅ ነው” በማለት ይህን የመጀመሪያውን የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ እንዲያበረታታና እንዲደግፍ ለሕዝቡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የመድረክ መሪው ጋዜጠኛ ሔኖክ በኢትዮጵያ ፕሬስ ዙሪያ ገለጻ የሰጠ ሲሆን  “የኢትዮጵያን የነጻ ፕሬስ ሚዲያ ታሪክ በሦስት እንደሚከፍለው ተናግሯል። አንደኛው  የድንጋጤ ዓመታት ፣ ሁለተኛው የመረጋጋት ዓመታት እና ሶስተኛው  ደግሞ የሽብር ዓመታት ናቸው ሲል ተናግሯል።

ድምጻዊ ተሾመ አሰግድ በየፕሮግራሙ ጣልቃ እየገባ ጣዕመ ዜማዎቹን እያሰማ በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበውን ሕዝብ ያዝናናው ሲሆን እሱም በበኩሉ ለኢሳት የሚገባውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ተሾመ “ኢሳት መረዳት ያለበት ተስፋ ያለው ሚዲያ ነው” በሚል የሙዚቃ መሣሪያዎቹን ክራይ ሁሉ በመቻል ይህንን ዝግጅት ካለምንም ክፍያ በማገልገል ለሌሎች ልማታዊ አርቲስቶች አረአያ የሚሆን ተግባር አከናውኗል።

የክብር እንግዳው ታማኝ በየነ ንግግሩን  የጀመረው የአክሊሉ ሃብተወልድን መልካም ተግባርና ለኢትዮጵያ ሐገራችን በዓለም አደባባይ የሰሩትን መልካም ተግባር አድንቆ “ይህ የኢሳት ፈንድራይዚንግን እዚህ እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት አክሊሉ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ዛሬ ልደታቸው ነበር” ብሏል። የአክሊሉ ሃብተወልድን መልካም ተግባር በቪድዮ እያስደገፈ አቅርቦ እኚህ ታላቅ ሰው በኋላ በስቅላት ሲገደሉ መንግስት ለሃገሪቱ ለፈጸሙት መልካም ተግባር እንኳ ሲል ይቅር አለማለቱን ወቅሷል።

አክሊሉ ሃብተወልድ በተወለዱበት ዕለት በሚኒሶታ የተደረገው ይህ የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ታማኝ በየነ “ኢሕአዴግን ትንሽ ልማው” በሚል ሕዝቡን በማሳቅ በተለይ በዘር ላይ ስለተመሰረተው የሕወሓት አገዛዝ በቪዲዮ ማስረጃ የተደገፈ ዘገባ በማቅረብ በአዳራሹ የተገኘውን ሕዝብ አስገርሟል። በተለይም “የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ከእያንዳንዱ የኢሕአዴግ ሚኒስተር ስር እንደታኮ የተቀመጡት ሚንስትሮች የትግራይ ተወላጆች ብቻ ናቸው” በማለት ምስላቸውን ከነሥራ ድርሻቸው በማቅረብ አሳይቷል። “የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች” በሚለው ቪድዮውም በአማካሪነት ያሉትን የትግራይ ተወላጆች በምስል አሳይቷል። የመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ያለውን የብሄር ተዋጽኦና የስልጣን ተዋረድንም በሚመለከት ባሳየው ቪድዮ ቁልፍ ቦታው በትግራይ ተወላጆች እንደተያዘ አጋልጧል።

በሚኒሶታ በተደረገው የኢሳት የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ ሕዝቡ በኪሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ሳንቲም ሳይቀር እያራገፈ ረድቷል።

የኢሳትን ፈንድራይዚንግ ለመታደም የመጣው ሕዝብ ቁጥር በሚኒሶታ ከቅንጅት በኋላ ከተደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ በቁጥሩ ከፍተኛው ሊባል የሚችል እንደሆነ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለ-ሐበሻ ድረ ገጽ ገልጸዋል። ይህም ኢሳት “ከምርጫ 97 በኋላ ሕዝብን ያነቃቃ ክስተት ተብሎ” የሚገለጸውን እውነት ያደርገዋል ይላሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide